የጤና ሚኒስቴር ከነሐሴ 15 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን 13ኛውን የምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
“የምሥራቅ አፍሪካን የጤና ኢኮኖሚ መገንባት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ጉባኤ በምሥራቅ አፍሪካ በጤናው ዘርፍ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት እና ጤናን ለሀገር ሉዓላዊነት እንዲሁም ለኢኮኖሚ የጀርባ አጥንትነት ለማድረግ ያለመ ነው።
በጉባኤው ላይ ከ20 በላይ ሀገራት የተውጣጡ 2 ሺህ መሪዎች፣ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት፣ ከእስያ እና ከመላው ዓለም የሚመጡ ከ30 በላይ ታዋቂ የሕክምና አምራች ድርጅቶች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ባለሀብቶች እና የፈጠራ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬሕወት አበበ እንዳብራሩት ጉባኤው በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ኢኮኖሚ ለማጠናከር፣ መድኃኒቶችን እና የሕክምና ቁሳቁሶችን በሀገር ውስጥና በቀጠናው በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም እንደ ሀገር አህጉራዊ ትስስርን በማጠናከር በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ማዕቀፍ ውስጥ የጤና የንግድ ሰንሰለቶችን በመፍጠር በጋራ ለመሥራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር በምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ትብብር የተዘጋጀው 13ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን በአድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
በሰናይት ሠይፉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: