Search

መሪን ከትውልድ ያስተሣሠረ፦ የቀይ ባሕር ታላቅ ትውልዳዊ ጥሪ

ማክሰኞ ነሐሴ 12, 2018 190

ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ እንደ እሳት ሲንቀለቀል፣ ሲብላላ እና ሲያብሰለስል የኖረ አንድ ጥልቅ ሕመም አለ፤ እሱም ከገዛ የተፈጥሮ የባሕር በራችን እና ከቀይ ባሕር ውኃ ዳርቻችን መነጠላችን ነው።

የኢትዮጵያ ታሪክ ገጾች በጉልህ እንደሚመሰክሩት፣ ሀገራችን በዓለም አደባባይ ገናና የነበረችው እና ታሪካዊ ጠላቶቿን ያርበደበደችው የባሕር በሮቿ በገዛ እጇ በነበሩበት ዘመን ነው።

ሆኖም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህን የሀገር ሕልውና፣ የደኅንነት እና የጂኦ-ፖለቲካ ጉዳይ ማንሣት፣ ስለ ቀይ ባሕር መጻፍም ሆነ መናገር ፍጹም "ነውር" ብሎም የሚያሳስር ወንጀል ተደርጎ ይቆጠርበት የነበረ አስከፊ ዘመን አሳልፈናል።

በዚያ ዘመን፣ ሀገር እንመራለን ይሉ የነበሩ የቀድሞ መሪዎች የሀገርን የደኅንነት እና የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነውን የወደብ ጉዳይ፣ "ወደብ ተራ ሸቀጥ ነው፣ ኪራያችንን ከፍለን እንጠቀማለን፣ ጎረቤት ሀገርን አናስቀይምም፣ ለጦርነት ልትዳርጉን ነው" በሚል ታላቅ የሉዓላዊነት ክብርን እንደ ተራ ሸቀጥ አቅልለው፣ ለሌሎች ኃይሎች ሲሞግቱ ተስተውሏል።

ትውልዱ የባሕር በር ቁጭቱን በውስጡ ይዞ፣ የልብ ሕመሙን እና እልሁን እንጉርጉሮውን አፍኖ፣ በዝምታ እንዲዘልቅ 30 ዓመታት ያህል ተፈርዶበት ነበር።

ሆኖም፣ ይህን የትውልድ ብሶት፣ የተዳፈነ እሳት ገና ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ በጠለቀ የሀገር ፍቅር እና ቁጭት ይረዱት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የዘመናችንን የፖለቲካ ታሪክ የለወጠ አዲስ ምዕራፍ ከፈቱ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ከባሕር መራቅ ያመጣባትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ስብራት እና የሎጂስቲክስ ጥገኝነት ገና ወደ ሥልጣን ሳይመጡ ጀምሮ በውል የተገነዘቡ መሪ በመሆናቸው፣ ያንን በሴራ የተገነባውን የፍርሃት ግድግዳ ከሥሩ ናዱት።

ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው ይዘውት የኖሩትን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በይፋ አደባባይ በማውጣት፣ የታፈነው የትውልዱ አንደበት ሆኑ። ዛሬ ላይ "የኢትዮጵያ መብት፣ ክብር እና ጥቅም መከበር አለበት" ብለው በግልጽ በመነሣት፣ ይህ ጉዳይ የብሔራዊ መግባባት አጀንዳ እንዲሆን ያደረጉት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ እና በታሪክ በወርቅ ቀለም ደምቆ የሚጻፍ እና የሚዘከር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የቀይ ባሕር ጉዳይ የጥቂት ፖለቲከኞች የጓዳ ወሬ መሆኑ ቀርቶ፣ 130 ሚሊዮን ሕዝብ የሕልውና አጀንዳ እንዲሆን አድርገዋል። በየመድረኩ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከምሁራን ጋር በሚያደርጉት ውይይት፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ሁሉ ላይ ሳይታክቱ እና ወደ ኋላ ሳይሉ ስለ ቀይ ባሕር በጽናት አንሥተዋል።

"የውኃው ጉዳይ የሕልውናችን መሠረት ነው" በማለት፣ ይህ ጂኦ-ፖለቲካዊ አጀንዳ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው፣ ምሁራን እንዲመራመሩበት፣ ሚዲያዎች እንዲዘግቡት እና ትውልዱ መብቱን ጠንቅቆ እንዲያውቅ አድርገዋል።

ይህ ድርጊታቸው፣ በዓለም ታሪክ ሀገራቸውን ከውድቀት ወደ ታላቅነት፣ ከውርደት ወደ ብሔራዊ ኩራት ከመሩ ታላላቅ የዓለም መሪዎች ጋር የሚያስመድባቸው ታላቅ ትውልዳዊ ተልዕኮ ነው።

አሜሪካን ለታላቅነት ያበቋት፣ ቻይናን የዓለም ኃያል ያደረጓት ታላላቅ መሪዎች፣ የሀገራቸውን የባሕር ላይ ተጽዕኖና ስትራቴጂያዊ በሮች ያስከበሩት ልክ እንደዚሁ ትውልድን ከኋላቸው በማሰለፍ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ዛሬ ለኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው ይህንን ብሔራዊ ተልዕኮ ከፊት ሆኖ የመምራት ታላቅ ኃላፊነት ነው።

ከሁሉም በላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንገድ ሌላውን ሀገር የመውረር፣ በጡንቻ የማስፈራራት ወይም በጉልበት የመንጠቅ አጀንዳ አይደለም። በተደጋጋሚ፣ በማያሻማ ቋንቋ እንዳሰመሩበት፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር መብቷን የምታረጋግጠው ፍትሐዊ፣ ሕጋዊ እና የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊ ጥቅም በማይጎዳ የጋራ ጥቅም (እርታ፣ ልርታ /Win-Win/) መርሕ ላይ ተመሥርታ ነው።

"አብረን እናድጋለን፣ ተደምረን እንበለጽጋለን፤ የተፈጥሮ ጸጋችንን በሰላማዊ መንገድ እናገኛለን" የሚለው ትውልዳዊ ጽኑ አቋም፣ የኢትዮጵያን ታላቅነት እና ሰላም ወዳድነት ለቀጠናውም ሆነ ለዓለም ያሳየ የብስለት ዲፕሎማሲ ነው። ይህ መርሕ የሀገራችንን ፍትሐዊ ጥያቄ በዓለም አደባባይ ተቀባይነት እንዲኖረው እና ብዙ ሀገራትም ከፍትሐዊ ጥያቄያችን ጎን እንዲቆሙ አድርጎታል።

ይህ ከመሪ እስከ ትውልድ የተሣሠረበት፣ ከላይ እስከ ታች አንድ ልብ የሆንበት የቀይ ባሕር አጀንዳ ዛሬ ፍሬ የሚያፈራበት፣ የትውልዱ ጥያቄ በተግባር መልስ የሚያገኝበት ጊዜ እጅግ ቀርቧል።

አሁን ላይ ይህንን የትውልድ ጥያቄ ማንም አያስቆመውም! ሀገራችን ታሪካዊ መብቷን የምታረጋግጥበት የንጋት ጮራ በግልጽ እየፈነጠቀ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሚና የትውልዱን ዐይን ገልጧል፤ የልብ ጩኸቱን ምላሽ ሰጥቷል፤ የድሉን ጎዳና ፍንትው አድርጎ ጠርጓል።

አሁን ትውልዱ ይህንን ዕድል በአግባቡ ተጠቅሞ ተባብሮ መቆም፣ ተደጋግፎ ብሔራዊ ጥቅሙን ማስከበር፣ የአፍራሽ ባንዳዎችን ተልዕኮ ማምከን ነው። ይህ ትውልድ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚችል ብቃት ያለው የትናንት የታሪክ ጉድለቶችን ማረም የሚችል የመደመር ትውልድ ነው።

የባሕር በራችን የሩቅ ሕልም አይደለም፤ የትውልዱ ጥያቄ ከመሪው ራዕይ ጋር ተጋምዶ ወደብ አልባነታችን በቅርቡ ታሪክ ይሆናል!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: