Search

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ከ18.5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እና የዳኞችን ሹመት በማፅደቅ መደበኛ ጉባኤውን አጠናቀቀ

ማክሰኞ ነሐሴ 12, 2018 123

የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 6 ዙር 5 የስራ ዘመን 10 መደበኛ ጉባኤውን በስኬት አጠናቅቋል።

ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ቆይታው ለክልሉ 2019 በጀት ዓመት ለልማት እና መልካም አስተዳደር እቅድ ማስፈጸሚያ የሚውል 18 ቢሊዮን 577 ሚሊዮን 523 ሺህ 685 ብር በጀት መርምሮ አጽድቋል።

ጉባኤው በቆይታው የክልሉ የአስፈፃሚ አካላት 2018 በጀት ዓመት 12 ወራት የልማት እና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶችን የሥራ ክንውን ሪፖርቶች በጥልቀት ገምግሟል።

ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ በክልሉ የፍትህ ሥርዓቱን ለማጠናከር የቀረበለትን 11 ዳኞች ሹመት መርምሮ በማፅደቅ የውሳኔ ሃሳቦችን አጽድቋል።

የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ መሰረት ማቲዎስ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ አበረታች ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አክለውም ያጋጠሙ ክፍተቶችን በማረም በአዲሱ የበጀት ዓመት የተሻለ ውጤትና ፈጣን ልማት ለማስመዝገብ በየደረጃው የሚገኙ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሚፍታህ አብዱልቃድር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: