Search

ኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሰራች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ዓርብ ነሐሴ 15, 2018 66

አፍሪካውያን በጤናው ዘርፍ ያላቸውን ጥገኝነት በመቀነስ የራሳቸውን ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስገንዝበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፣ 13ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽንን ዛሬ በአዲስ አበባ በይፋ በከፈቱበት ወቅት ነው።

በዘመናችን የሉዓላዊነት ትርጉም ከፖለቲካዊ ወሰን ያለፈ፣ የሕዝብን ጤና የመጠበቅ አቅምን ያካተተ መሆኑን ያስገነዘቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "የማምረት አቅም የሌለው ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት ሙሉ ሊሆን አይችልም" ብለዋል።

የአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት በውስጥ አቅም ካልተገነባ ደካማ ሆኖ እንደሚቀር ጠቅሰው፣ የጤና ሉዓላዊነት መገለጫዎች እናቶችን የመንከባከብ፣ ለህጻናት የሚያስፈልጉ መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን የማሰልጠንና የማቆየት አቅም መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች አህጉሪቱ ለክትባት፣ ለመድኃኒቶችና ለሕክምና መሳሪያዎች ባላት ጥገኝነት ምክንያት ምን ያህል ተጎጂ እንደነበረች ማሳየታቸውን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አፍሪካውያን የዓለምን ውሳኔ ሳይጠብቁ ወረርሽኝን የመቋቋም አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህንን እውን ለማድረግም ኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

አዲስ አበባን ለአፍሪካውያን ቀዳሚ የሕክምና ቱሪዝም እና የከፍተኛ ሕክምና ማዕከል ማድረግ፣መድኃኒቶችንና የሕክምና መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት እንዲሁም በመንግሥትና በግል ዘርፍ መካከል ያለውን አጋርነት ማጠናከር የኢትዮጵያ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከችግር መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣይ ቀውሶች ዝግጁ የሆኑ የጤና ሥርዓቶችን መገንባት እና የውጭ ጥገኝነትን ማስወገድ ጊዜ የማይሰጠው አህጉራዊ ግዴታ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አመላክተዋል።

በአሸናፊ እንዳለ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: