ኢትዮጵያ በ76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ጉባኤ ላይ የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ያከናወነቻቸውን ስኬታማ ተግባራት ተሞክሮ አድርጋ እንደምታጋራ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለፁ፡፡
76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ (RC76) ከነሐሴ 18 - 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
በጉባኤው ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሰራች ያለውን ስራ በተሞክሮነት የምታጋራበት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ካንትሪ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መሀመድ ጃናቢ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን አህጉራዊ ጉባኤ ለ4ኛ ጊዜ የምታዘጋጅ ሲሆን፣ በጉባኤው ከ47 የአፍሪካ አባል ሀገራት የተወጣጡ የጤና ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሕዝብ ጤና ባለሙያዎች እና የልማት አጋሮችን ጨምሮ ከ800 በላይ ተሳታፊዎች በመገኘት በ1.5 ቢሊዮን ህዝብ የጤና ሁኔታ ላይ የሚያተኩሩ የጋራ መፍትሔዎችን ይመክራሉ።
በመድረኩ ኢትዮጵያ ዘላቂ የጤና ፋይናንስ ስርዓት መገንባት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎትን ማጠናከር፣ የዲጂታል ጤና ስርዓትና በሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅምን ማሳደግ ላይ የነበራትን ስኬታማ ተሞክሮዎች የምታጋራ ይሆናል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ካንትሪ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መሀመድ ጃናቢ ኢትዮጵያ የማርበርግ ወረርሽኝን በፈጣን ሁኔታ የተቆጣጠረችበትን መንገድ በማደነቅ፣ ይህ ጉባኤ አፍሪካን ከተጋላጭነት ወደ አይበገሬነት እንዲሁም ከተረጅነት ወደ ራስን መቻል ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ መፍትሔ የሚያስቀምጥ ታሪካዊ መድረክ መሆኑን አብራርተዋል።
በብሩክ ተስፋዬ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: