ዓለም በፍጥነት ወደ ዲጂታል ዘመን እየተሸጋገረች ባለችበት ወቅት፣ የአንድ ሀገር የወደፊት ተወዳዳሪነት የሚወሰነው ባላት የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎቿ ባላቸው ዕውቀትና ክህሎት ነው።
በዚህ የለውጥ ሂደት ኢትዮጵያ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ባሻገር የራሷን የዲጂታል አቅም በመገንባት ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመሸጋገር እየሠራች ትገኛለች።
የዚህ ሽግግር ዋና መሠረት የሰው ኃይል ነው። ቴክኖሎጂን መጠቀም ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂን መፍጠር፣ ችግርን በዲጂታል መንገድ መፍታት እና እውቀትን ወደ ኢኮኖሚያዊ እሴት መቀየር የሚችል ትውልድ መገንባት ወሳኝ ነው።
በዚህ አቅጣጫ የተጀመረው በሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶችን የዲጂታል ክህሎት ባለቤት የማድረግ ጥረት ከአንድ የሥልጠና ፕሮግራም በላይ የሆነ ሀገራዊ የለውጥ አቅጣጫ ነው።
7 ሚሊዮን ኮደሮች የሚለውም ቁጥር ብቻ ሳይሆን የሐሳብ፣ የፈጠራና የኢኮኖሚ አቅምን የሚወክል ግብ ነው። አንድ ወጣት ኮዲንግ ሲማር በኮምፒዩተር ላይ ኮድ መጻፍን ብቻ ሳይሆን፤ ችግርን መተንተን፣ መፍትሔ መንደፍ፣ ሐሳብን ወደ ምርት መቀየር እና የራሱን የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል አቅም ያገኛል።
ይህም ኢትዮጵያን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ ቴክኖሎጂ ፈጣሪነት ለማሸጋገር የሚያግዝ እድል ነው። የዲጂታል ክህሎት ያለው ወጣት ለራሱ ሥራ ከመፍጠር ባሻገር ለሌሎችም የሥራ እድል ይፈጥራል።
በተለይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) መስፋፋት ይህንን ሽግግር የበለጠ አፋጥኖታል። ከመረጃ ትንተና እስከ ጤና፣ ከግብርና እስከ ትምህርት የዘለቀ አዳዲስ የችግር መፍቻ መንገዶችን እያስገኘ ነው።
በዚህ ዘርፍ የሚፈጠረው እውቀት ኢትዮጵያ የራሷን ቴክኖሎጂ እንድታበለጽግ እና በአፍሪካና በዓለም ዲጂታል ገበያ ውስጥ የበለጠ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያግዛል።
ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስንሸጋገርም ትኩረቱ ዲጂታል አገልግሎት ከማስፋፋት ባሻገር የሚፈጥር የሰው ኃይልን ማብዛት ላይ ነው። የተማረ ወጣት የሚፈጥረው ሶፍትዌር፣ የሚያበለጽገው መተግበሪያ፣ የሚያቀርበው ዲጂታል አገልግሎት እና የሚፈጥረው የዲጂታል ኢኮኖሚው ተጨባጭ ውጤቶች ናቸው።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ ከኮምፒዩተር እና ከኢንተርኔት የሚጀምር ቢመስልም፣ ትልቁ መሠረት ሰው ነው። ዛሬ የሚማረው ክህሎት ነገ የሚፈጠረው ምርት ነው፤ ዛሬ የሚወጣው ሐሳብ ነገ የሚመሠረተው ኩባንያ ነው፤ ዛሬ የሚገነባው የዲጂታል አቅም ነገ የሀገር ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት ነው።
ስለዚህ ከዲጂታል ክህሎት ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚደረገው ጉዞ ከተጠቃሚነት ወደ ፈጠራ፣ ከእውቀት ወደ እሴት፣ ከሥራ ፈላጊነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት እና ከአካባቢያዊ ገበያ ወደ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚወስድ የኢትዮጵያ የነገ ጉዞ ነው።
7 ሚሊዮን ኮደሮችም የዚህ ጉዞ ቁጥር ብቻ ሳይሆኑ፣ የነገዋን ዲጂታል ኢትዮጵያ የሚገነቡ ሚሊዮን አዕምሮዎች ናቸው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: