አንድ ከተማ ዘመናዊ ስትሆን የሚታዩት ከፍተኛ ህንፃዎች፣ ሰፊ መንገዶችና ዲጂታል አገልግሎቶች ብቻ አይደሉም፤ ከመሬት በታች የሚሰሩ ነገር ግን ለእይታ ግልፅ ያልሆኑ የውሃና ፍሳሽ እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች የዘመናዊ ከተማ መሠረት ናቸው።
በአዲስ አበባ ከመሬት በላይ ከተገነቡት መሰረተ ልማቶች እኩል ከመሬት በታችም ተገንብተዋል።
ንፁህና ጤናማ አካባቢ፣ የተሻለ የፍሳሽ አገልግሎት፣ የተቀነሰ የትራፊክ መዘጋትና የተሻለ የከተማ ኑሮ ሲገነባ በመሬት ላይ የሚታየው ውጤት ከመሬት በታች በሚሰራው ቴክኖሎጂ ይጀምራል።
አዲስ አበባ ወደ ስማርትና ዘመናዊ ከተማ በምትሸጋገርበት ጉዞ ላይ ማይክሮ ተነሊንግ ከሰው ሕይወት እስከ ከተማዋ የወደፊት ልማት የሚዘልቅ የቴክኖሎጂ አቅም ነው።
ዛሬ አዲስ አበባ በሕዝብ ቁጥርና በከተማ እድገት እየሰፋች በመሆኗ ከተማዋን ንፁህ፣ ጤናማና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የፍሳሽ መሠረተ ልማት ማስፋፋት ወሳኝ ሆኗል። በዚህ ሂደት ማይክሮ ተነሊንግ ቴክኖሎጂ ከሰው ሕይወት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ዘመናዊ መፍትሔ እየሆነ ይገኛል።
የዚህ ቴክኖሎጂ ትልቁ ጥቅም የከተማዋን ዕለታዊ እንቅስቃሴ ሳይቋርጥ አስፈላጊውን የፍሳሽ መስመር ከመሬት በታች ማስቀመጥ መቻሉ ነው። በቀድሞ አሠራር የፍሳሽ መስመር ትልቅ መንገድ ለማሻገር ወይም ሌላ መሠረተ ልማት ለማቋረጥ መንገድ መቆፈር/መቁረጥ/ የተለመደ ነበር። መንገድ ሲቆረጥ ደግሞ የትራፊክ መጨናነቅ፣ የንግድ ሥራ መስተጓጎልና የነዋሪዎች ጊዜ መባከን ይፈጠራል።
ማይክሮ ተነሊንግ ይህንን ውስብስብ ችግር የሚፈታ በከተማዋ ላይ ትልቅ ቁፋሮ ሳይደርግ ሥራውን ከመሬት በታች በመፈጸም የነዋሪውን ጊዜ፣ የንግድ እንቅስቃሴና የከተማዋን ትራፊክ ፍሰት እንዲሳለጥ የሚያደርግ ነው።
ይህንን ዘመናዊ አሠራር በመጠቀም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አሁን በከተማዋ ውስብስብ የሆኑ የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከእነዚህ ሥራዎች መካከል የባቡር ሀዲድን ማቋረጥ የሚጠይቁ ከባድ የፍሳሽ መስመር ዝርጋታዎችም ይገኙበታል።
የማይክሮ ተነሊንግ ስራ በከተማዋ እየተሰራ ያለው የምስራቅ ተፋሰስ ፍሳሽ መሰረተ ልማት አካል የሆነው በመገናኛ ደራርቱ ህንጻ ወረድ ብሎ ያለው የ55 ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር ሀዲድ እና የአስፓልት መንገድ እንዲሁም ከሲኤም ሲ ቤቶች ወደ አለምዓቀፍ ኮንቬሽን ሴንተር የሚያሻግረው የ92 ሜትር ርዝመት ያለው ውስጥ ለውስጥ በመቦርቦር 600 ሚሊ ሜትር ዲያሜትር ስፋት ያለው የፍሳሽ መስመር ዝርጋታ ስራ ተጀምሮ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡
ይህ በከተማዋ የሚታየው ቴክኖሎጂን በመሠረተ ልማት ሥራ ላይ የማዋል አቅም ከፍ እያለ መምጣቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ አዲስ አበባም የነገዋን ከተማ በቴክኖሎጂ እየገነባች መሆኗን እንደሚያረጋግጥ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: