የሀገር ዕድገት የሚለካው ዛሬ በምንኖረው ዕለታዊ ህይወት ብቻ ሳይሆን፣ ለሚመጣው ትውልድ በምናስረክበው ጠንካራ መዋቅራዊ መሰረት ጭምር በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተከናወኑ ያሉ የከተሞች ልማትና የመታደስ ሥራዎች ከኮንክሪትና ህንፃ ግንባታ ባለፈ ጥልቅ የትውልድ ግንባታ እና የማህበራዊ ፍትህ እሴትን የያዙ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ከተማን ማልማት ለልጆቻችን መልካም ሀገር ጥሎ መሄድ ነው፤ ልጆቻችን ሌላ ናፋቂ ሳይሆኑ በሀገራቸው የተሻለ አካባቢ ኖሯቸው እንዲቀጥሉ ማስቻል ነው” ሲሉ እንደተናገሩት፣ ከተሞችን ማልማት በትውልዶች ዘንድ የሥነ-ልቦና የበላይነትና የባለቤትነት ስሜት ይፈጥራል።
ህፃናት እና ወጣቶች ፅዱና ዘመናዊ መሠረተ-ልማት በተዘረጋላቸው አካባቢዎች ሲያድጉ በሀገራቸው የመኩራትና የማሰብ አቅማቸው የሚጎለብት ሲሆን፣ ይህም የሌሎችን ሀገር ዕድገት በምሥል እያዩ ከመመኘት ይልቅ በገዛ ሀገራቸው የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።
በአሁኑ ወቅት በስፋት የሚተገበሩት የኮሪደር ልማቶች እና የአረንጓዴ ስፍራዎች ማስፋፊያ ጊዜያዊ የውበት ሥራዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የህፃናት መጫወቻ ፓርኮች፣ ምቹ የእግር መንገድ፣ የብስክሌት መስመሮች እና አረንጓዴ ስፍራዎች መፈጠራቸው ለአየር ንፅህና፣ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ እና ለአዕምሯዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንቶች ናቸው።
በተጨማሪም ንፁህና የተቀናጀ የከተማ መዋቅር የአገልግሎት ዘርፍን ያነቃቃል፣ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል እንዲሁም የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት ፍሰትን በመሳብ ወጣቶች ስደትን ብቸኛ አማራጭ አድርገው እንዳይወስዱ ያደርጋል።
በመሆኑም እያንዳንዱ በየአካባቢያችን የምናደርገው የልማት፣ የፅዳት እና የተፈጥሮ እንክብካቤ እንቅስቃሴ ለልጆቻችን የምናስቀምጠው ዘላቂ ሀብትና የማይጠፋ ታሪካዊ ዐሻራ በመሆኑ፣ ዘላቂ የከተሞች ልማት የወላጅነትም ሆነ የዜግነት ትልቁ ሀገራዊ ኃላፊነታችን ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: