Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን የSTEM ፕሮግራም ተማሪዎች አስመረቀ

ዓርብ ነሐሴ 15, 2018 68

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲያካሂድ የቆየው STEM (ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ማቴማቲክስ) የስልጠና ፕሮግራም የመዝጊያ እና የተማሪዎች ምረቃ ስነ-ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቺፍ ኦፕሬሽን ዘርፍ ዋና ኃላፊ አቶ ረታ መላኩ የስልጠናው ዋና ዓላማ ለወጣቶች በአቪዬሽን፣ በዲጂታልና በቴክኒክ ዘርፎች ዘመናዊ አቅምን በበመፍጠርና በማቅረብ ተተኪ ባለሙያዎችን ማፍራት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር የተደረገው ይህ የረጅም ጊዜ አጋርነት ወጣቶች ገና ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ ትልልቅ ህልሞችን እንዲልሙና የወደፊት የሙያ ጎዳናቸውን እንዲለዩ ትልቅ ድጋፍ ማድረጉን አብራርተዋል።

በስልጠናው ወቅት የታየው የወጣቶች የፈጠራ ችሎታና ቁርጠኝነት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ብሩህ ተስፋ አስተማማኝ እጆች ላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ያሉት አቶ ረታ፤ ተመራቂዎች በቀሰሙት እውቀት ትርጉም ያለው አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ ጥሪ በማቅረብ የመልካም ምኞት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር STEM ዴስክ ኃላፊ አቶ ታደሰ ተሬሳ በበኩላቸው፤ ተማሪዎቹ የጀመሩት ጉዞ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ከእነሱ በኋላ ለሚመጡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተማሪዎች መንገድ የሚከፍትና ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ተማሪዎች ያገኟቸውን የስልጠና እውቀቶች እለት ተእለት በቴክኖሎጂ እየደገፉ ከዋና የፊዚክስ ኬሚስትሪ እና ባዮሎጂ ትምህርታቸው ጋር አገናኝተው ወደ ተግባር በመቀየር ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአፍሪካ የቦይንግ ዳይሬክተር አምባሳደር ሄኖክ ሻወል በበኩላቸው፤ ተማሪዎቹ ባለፉት 6 ሳምንታት በነበራቸው ቆይታ በኮዲንግ ሮቦቲክስ እና በዘመናዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ የመጀመሪያ ደረጃ ተግባራዊ ክህሎት ማግኘታቸውን በሳይንስ ሙዚየም የሚገኘውን ቋሚ የአቪዬሽን ኤግዚቢሽን የመጎብኘትና ከቀድሞ ተመራቂዎች ጋር የልምድ ልውውጥ የማድረግ እድል ማግኘታቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ላዕከ ታደሰ፤ ከመላው ኢትዮጵያ የተወጣጡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች "STEM" የትምህርት መርሃ ግብር አማካኝነት 6 ሳምንታት ሥልጠና ሲከታተሉ ቆይተዉ ከቴክኒክ እውቀት ባሻገር የቡድን ሥራ ሂሳዊ አስተሳሰብ ችግር ፈቺነት እና የፈጠራ ክህሎትን ማዳበር የሚያስችላቸው ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: