በአሜሪካ ኔቫዳ እና አሪዞና ግዛቶች መካከል የሚገኘውና በሁቨር ግድብ ምክንያት በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የተፈጠረው ግዙፉ ሜድ ሰራሽ ሐይቅ ከ2020 ጀምሮ በደረሰበት ከፍተኛ የውሃ መጠን መቀነስ ምክንያት ለአስርተ ዓመታት በውስጡ የቀበራቸውን በርካታ አስደናቂና አስገራሚ ምስጢራት ይፋ ማድረጉን ቀጥሏል።
በአሜሪካ የውሃ ልማት አባት በኤልዉድ ሜድ ስም የተሰየመው ይህ ታሪካዊ ሐይቅ፣ የውሃ መጠኑ ታሪካዊ ወደሆነ ዝቅተኛ ደረጃ መስመጡን ተከተሎ ከውሃ ቀውስ ባሻገር የሰው ቅሪቶችን፣ የወታደራዊ አውሮፕላን ፍርስራሾችን እና የታሪካዊ ከተሞችን ቅሪት ለአለም እያሳየ ይገኛል።
በአውሮፓውያኑ ግንቦት 1 ቀን 2022 በሐይቁ ሄሜንዌይ ሃርቦር አካባቢ ከተጋለጠ ብረት በርሜል ውስጥ በጥይት ተመቶ የተገደለ የሰው አፅም የተገኘ ሲሆን፣ መርማሪዎች አሰቃቂው ግድያ በ1970ዎቹ ወይም 80ዎቹ በላስ ቬጋስ የወንጀል ዓለም ዘመን የተፈጸመ መሆኑን ቢገምቱም የሟቹ ማንነት እስካሁን በይፋ አልተረጋገጠም።
በቅርቡም የሐይቁ ውሃ መጠን ወደ 1,040.5 ጫማ ዝቅ ማለቱን ተከተሎ ተጨማሪ የሰው መንጋጋ እና የአጥንት ክፍሎች የተገኙ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በዲኤንኤ ምርመራ በ2002 እና በ1974 በሐይቁ ውስጥ ሰጥመው የሞቱ ሰዎች ማንነት መረጋገጡ ይታወሳል።
ከእነዚህ አስፈሪ ግኝቶች በተጨማሪ ሐይቁ የሳይንስ እና የአቪዬሽን ታሪክ ማህደር መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ሁነቶች ተገልጠዋል።
በአውሮፓውያኑ 1948 የከባቢ አየርና የኮስሚክ ሬይ ሳይንሳዊ ምርምር በማካሄድ ላይ እያለ ወደ ውሃው በጣም ዝቅ ብሎ በመብረሩ ምክንያት ስጥሞ የነበረው B-29 Superfortress የተባለው ታዋቂ ወታደራዊ አውሮፕላን ፍርስራሽ ከአደጋው ከ55 ዓመታት በኋላ በ2003 ተገኝቶ በብሄራዊ ፓርክ አገልግሎት ተመዝግቦ ይገኛል።
እንዲሁም በ1930ዎቹ በውሃ የተሸፈነው የቀድሞው የቶማስ ሰፈር ፍርስራሽ የውሃው መጠን ሲቀንስ እንደገና መታየቱ፣ ሜድ ሐይቅ ከቀላል የውሃ ማጠራቀሚያነት ባለፈ የሰዎች የግል ታሪክ፣ የሳይንስ እና የወንጀል ምርመራ ህያው ማህደር መሆኑን ያረጋገጠ ድንቅ ስፍራ አድርጎታል።
በሲሳይ መንግስቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: