Search

ጎቤ እና ሽኖዬ፦ የኦሮሞ ሕዝብ የልምላሜ፣ የማንነት እና የባህል ውበት መገለጫዎች

ዓርብ ነሐሴ 15, 2018 72

ባህል የማህበረሰብ ማንነት መስተዋት፣ የትውልድ መያያዣ ድልድይ እና የታሪክ ህያው ምስክር ነው።

የኦሮሞ ህዝብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሸጋገራቸው በርካታ ሀገር በቀል እሴቶች እና ባህላዊ ስርዓቶች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በገዳ ስርዓት ውስጥ የራሳቸው የሆነ ልዩ ቦታ እና መልእክት ያላቸው፣ የክረምቱን መውጣት እና የመጸውን መግባት የሚያበስሩት የጎቤ እና ሽኖዬ ባህላዊ ጨዋታዎች ተጠቃሾች ናቸው።

በኦሮሞ የገዳ ስርዓት የጥሞና ወቅት ተደርጎ ከሚወሰደው ወርሃ ክረምት ወደ የተስፋ እና ልምላሜ ምልክት ወደ ሆነው የመጸው ወቅት ሲሸጋገር፣ የተለያዩ መልእክቶች ያሏቸው የምስጋና እና ባህላዊ የጨዋታ ስርዓቶች ይከናወናሉ።

ለታላቁ የምስጋና እና የመሰባሰቢያ በዓል እሬቻ መዳረሻነት በወጣቶች ዘንድ የሚዘወተረው የጎቤ እና ሽኖዬ ባህላዊ ጨዋታ ከጭጋጋማው የክረምት ወቅት ወጥተው ውብ የሆነውን የመጸው ወቅት ለመቀበል ወንዶች (ቄሮ) እና ልጃገረዶች (ቀሬ) በባህላዊ አልባሳት አጊጠው በደስታ የሚጫወቱበት ድንቅ ባህላዊ ስርዓት ነው።

 

በነሐሴ እና ጳጉሜ ወራት ወጣቶች በየአካባቢው እና በየመንደሩ በመሰብሰብ የሚያከብሩት ይህ ባህል የደስታ፣ የአንድነት እና የማህበራዊ ቁርኝት ምልክት ሲሆን፣ የትውልድን ክብር፣ ብሔራዊ ኩራትን እና የተፈጥሮን ውበት የሚያንጸባርቅ ጥልቅ ጥበብ ነው።

እነዚህ ባህላዊ ጨዋታዎች የኦሮሞን ታሪክ እና ማንነት ለአዲሱ ትውልድ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን፣ እየተረሱ የመጡ እሴቶችን ለመመለስ፣ የማህበረሰብ ግንኙነትን ለማጠናከር እና የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና አላቸው።

በመሆኑም እንደነዚህ ያሉ ውብ እሴቶችን ጠብቆ ማቆየት፣ ለአዲሱ ትውልድ ማስተላለፍ እና ከዘመናዊ የቱሪዝም ዘርፉ ጋር አያይዞ ማስፋፋት የመላው ማህበረሰብ እና የሚመለከታቸው አካላት ቀዳሚ ሀላፊነት በመሆኑ፣ ጎቤ እና ሽኖዬን የመሰሉ ህያው ሀብቶቻችንን የማንነታችን መገለጫ አድርገን ልንከባከባቸው እና ልናስተዋውቃቸው ይገባል።

በሀይማኖት ከበደ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: