Search

ኢትዮጵያን የቤተሰብ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሚሰራው ሳዑዲያዊው የይዘት ፈጣሪ አሊ ዳውድ

ዓርብ ነሐሴ 15, 2018 74

ታዋቂው የሳዑዲ አረቢያ የይዘት ፈጣሪ፣ ፎቶግራፈር እና ተጓዥ አሊ ዳውድ ሀዳድ ኢትዮጵያን ለዓረብ እና ለሳዑዲ አረቢያ ቤተሰቦች ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

ወደ ኢትዮጵያ ያደረጋቸውን ተደጋጋሚ ጉብኝቶች እና የኢትዮጵያን የቱሪዝም እድገት አስመልክቶ ለኢቢሲ ዶትስትሪም አስተያየቱን የሰጠው አሊ ዳውድ፣ በቅርቡ ከቤተሰቡ ጋር ያደረገው ጉብኝት የዚሁ አዲስ ምዕራፍ ማሳያ መሆኑን አመልክቷል።

በአውሮፓውያኑ 2016 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ይህ ይዘት ፈጣሪ ቀደም ሲል ስለ ኢትዮጵያ የነበረው አሉታዊ ግንዛቤ በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ባህር ዳር፣ ጣና ሐይቅ፣ የዓባይ ፏፏቴ እና ሀዋሳ ባደረጋቸው ጉብኝቶች ሙሉ በሙሉ እንደተቀየረ ተናግሯል።

እንደ ፎቶግራፈርነቱ ከወንጪ እስከ አፋር ባለው መሬት ላይ አስደናቂ የተፈጥሮ ውበት መመልከቱን የገለጸው አሊ ዳውድ፣ በቢላል አል-ሀበሺ ሙዚየም ባደረገው ጉብኝትም የነቢዩ ሙሐመድ (..) ባልደረቦች በኢትዮጵያ ያገኙትን መልካም አቀባበል እና የኢትዮጵያን ታሪካዊ እሴት አድንቋል።

ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ በየወሩ የሚታይ መሆኑን ጠቅሶ፣ እንደ ወዳጅነት፣ አንድነት እና እንጦጦ ፓርክ ያሉ ዘመናዊ መዝናኛዎች ለትልቅ የቤተሰብ ቱሪዝም ዝግጁ መሆኗን እንደሚያሳዩ ገልጿል።

በተጨማሪም የዓረብኛ ቋንቋ አገልግሎት እንዲስፋፋና የቱሪስት መሪዎች ቁጥር እንዲበራከት የጠየቀ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) መሪነት ለኢትዮጵያ የቱሪዝም እድገት የተጀመረው ተነሳሽነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሷል።

በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: