Search

ኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟን እያሳደገች ነው - ዶክተር መቅደስ ዳባ

ዓርብ ነሐሴ 15, 2018 69

ኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟን እያሳደገች መሆኗን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

13ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጤና አጠባበቅ ፌዴሬሽን ኮንፍረንስ እና ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን "በምሥራቅ አፍሪካ የማይበገር የጤና ኢኮኖሚ መገንባት" በሚል መሪ ሐሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟን እያሳደገች መሆናን ገልጸው፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ጠንካራ የጤና ተቋማትን መገንባት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በአፍሪካ እንደ ኢቦላ ዓይነት ወረርሽኝ፣ የጤና ደኅንነት፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ውስንነት የጋራ ስጋት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ አፍሪካውያን በጋራ መሥራት ይገባናል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ኢትዮጵያ በጤና አጠባበቅ መሰረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና ተቋም መገንባቷን ገልጸው፣ በጤና ቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀብት ልማትና በመሰረታዊ የጤና መለኪያዎች ላይ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።

ውጤቱ በመንግሥትና የግሉ የጤና ተቋማት ዘርፍ የመጣ እንደሆነና መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፣ የዲጂታል ጤና ሥርዓት ምርጫ ሳይሆን አፍሪካውያን ብሔራዊ የጤና አጀንዳቸው ሊያደርጉት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ደረጃ ሦስት ማግኘቷን በማንሳት፣ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያዎችን ማምረት ቁልፍ አጀንዳዋ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአፍሪካን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል ትብብር ወሳኝ እንደሆነና ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር የምታደርገውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: