በፖለቲካ ትግል ውስጥ ጊዜያዊ ኩርፊያ እና ስሜታዊነት ታሪካዊ ስህተት ላይ ሲጥሉ ማየት የተለመደ ቢሆንም፣ የህዝብን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ጥምረት መፍጠር ግን ከስህተትም ያለፈ ታሪካዊ ክህደት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ትጥቅ አንስተው ጫካ የገቡ ሀይሎችን እሳቤ በደራሲ ከበደ ሚካኤል ተረት መስለው አቅርበውታል።
ከእናቷ ጋር በተፈጠረ ኩርፊያ ከጉድጓድ የወጣችው አይጥ ለእርሷ የተሻለ ወዳጅ መስሏት የዘላለም ጠላቷ ወደሆነው ድመት ስታመራ ከላይ ደግሞ ሌላ ጠላት ጭልፊት እያንዣበበባት መሆኑን ሳታውቅ ለጥፋት መዳረጓን አብራርተዋል።
እናም ዛሬ ላይ “ለህዝብ መብት እንታገላለን” በሚል ጫካ የገቡ ሃይሎች እግራቸው እየመራቸው ያለው ወደ ትናንቱ ታሪካዊ ጠላታቸው ደጅ መሆኑን ገልጸዋል።
ለእነዚህ ሃይሎች የጦር መሳሪያ የሚያስታጥቀው፣ ከለላ የሚሰጠው እና የሴራ ማዕከል የሆነው አካል ህዝቦችን በጠላትነት የፈረጀ፣ ኢትዮጵያን የባህር በር አሳጥቶ የጂኦግራፊ እስረኛ ያደረገ እና ብሄሮችን እርስ በእርስ በማጋጨት ደም ያቃባ ታሪካዊ ጠላት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ከዚህ አካል ጋር የሚደረግ ማንኛውም አይነት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊ ትብብር ውጤቱ ጥፋትና ሞት እንጂ ልማት ሊሆን የማይችል “ያልተቀደሰ ጋብቻ” መሆኑን በመግለፅ፣ የትናንቱን የጥፋት ታሪክ ዛሬ ላይ ለመድገም የሚደረገው መፍጨርጨር በጊዜ ካልታረመ በህዝቦች ላይ ሰቆቃ ከማድረስ የዘለለ ውጤት እንደማይኖረው አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ህዝቦችም ሆኑ ልሂቃኑ ይህንን ታሪካዊ መሰረት የሌለውና የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ አካሄድ በጊዜ ሊያስቆሙት እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: