“ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ” በመባል የሚታወቀው የቱሪዝም ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገትና ለብሄራዊ ገፅታ ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ እንደመሆኑ መጠን፣ ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ የማይዳሰሱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች መካከል በየአመቱ ከነሐሴ 15 እና 16 ጀምሮ በደማቅ ሁኔታ የሚከበሩትና የሴቶች የነፃነት አደባባይ በዓላት የሆኑት ሻደይ፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬ እና ሶለል ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው።
እንደየአካባቢው አጠራር ልዩነት ያላቸው እነዚህ በዓላት ቃሉ ትርጉም ለምለም እርጥብ ሳር ከሚለው ስያሜያቸው ጀምሮ የክረምቱን መገባደጃና የፍጥረት እድሳት የሚያበስሩ ውብ የጋራ እሴቶች ናቸው።
በበዓሉ ወቅት ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች በባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ተውበው፣ ሳሩን በወገባቸው በማሰር በዜማና በጭፈራ አደባባዮችን ያደምቃሉ።
በዓሉ የሴቶች ነፃነት የሚገለፅበት ቢሆንም፣ ወንዶችም ከነሐሴ መጀመሪያ ጀምሮ ፀጉራቸውን “ባጠቋ” በተባለ ተፈጥሮአዊ ቅባት በመቀባት፣ ለሴቶች የሚሆን ሳር “በባዶ ሆዳቸው” በመቁረጥና “ጊጤ” በተባለ ግንድ ላይ የጦር ውድድር በማድረግ ድጋፋቸውንና ጥንካሬያቸውን ያሳያሉ።
በተጨማሪም ሴቶች በቤት ውስጥ የሚሰሩትን “አስኩር” የተሰኘ ምግብ ወንዶች ለማግኘት በሚያደርጉት ወዳጃዊ ትግልና በዓሉ ሲጠናቀቅ በሚከናወኑ ስነ-ስርዓቶች የማህበረሰቡ ፍቅር፣ መተሳሰብና ትዳር የመመስረት ባህላዊ እሴቶች በጎላ ሁኔታ ይንጸባረቃሉ።
እነዚህ የደስታና የፍቅር መገለጫዎች የሆኑ ሀገር በቀል ቅርሶች የህዝባችንን ታሪክና የአንድነት መንፈስ የሚያንፀባርቁ በመሆናቸው፣ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሊኮራባቸው፣ በአግባቡ ሊጠብቃቸውና ለቀጣዩ ትውልድ በክብር ሊያስተላልፋቸው ይገባል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: