በደቡባዊ ጣሊያን የምትገኘውና በልዩ ባህላዊና ማህበራዊ ህይወቷ የምትታወቀው የሲሲሊ ደሴት፣ በአውሮፓ በከፍተኛ ሙቀቷ በሚታወቀው ፍሎሪዳ ከተማዋ አማካኝነት በሙቀት ማዕበል እየተፈተነች ትገኛለች።
በተለይም ነዋሪዎቿ ከቤት ውጭ ተሰባስበው፣ ወንበር ይዘው በደጃፋቸው በመቀመጥ አየር የሚወስዱበትና ከጎረቤቶቻቸው ጋር የሚያወሩበት ጥንታዊ ማህበራዊ ባህል በዚህ ከባድ ሙቀት ምክንያት አደጋ ላይ ወድቋል።
በ2021 እስከ 48.8 ዲግሪ ሴልሺየስ የሚደርስ ከፍተኛ የአውሮፓ የሙቀት ሪከርድ የተመዘገበባት ይህች ከተማ፣ አሁን ላይ ነዋሪዎቿን ከቤት እንዳይወጡ በማድረግ በኮቪድ-19 ወቅት ከነበረው የማህበራዊ መገለል ጋር የሚመሳሰል ምስል እያሳየች ይገኛል።
ቀን ቀን መንገዶቿና የህዝብ መሰብሰቢያዎቿ ባዶ የሚሆኑ ሲሆን፣ ሙቀቱ እስከ ሌሊት ድረስ ባለመቀነሱ ምክንያት የነዋሪዎች እንቅልፍና እረፍት ተረብሿል።
ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ከሰዎች የዕለት ተዕለት ነፃነትና ማህበራዊ ግንኙነት በተጨማሪ በጤና እና በኢኮኖሚ ላይም ከባድ ጫና እያሳደረ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኙ ንብ አናቢዎች በሙቀቱ ምክንያት የንብ መንጋዎቻቸውን በማጣታቸው ከፍተኛ የገቢ ኪሳራ እንደገጠማቸው የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።
የፍሎሪዳ ሁኔታ የሚያሳየው የአየር ንብረት ለውጥ ከቁጥር መጨመር በላይ የሰዎችን ማህበራዊ ህይወትና የቆየ ባህል ሙሉ በሙሉ የመቀየር አቅም ያለው ከባድ ተፈጥሯዊ ፈተና መሆኑን ነው።
በስምረት ገዛኸኝ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: