Search

የሻምፒዮኖች ፍልሚያ በቪላ ፓርክ አርሰናል ድሉን ለማስቀጠል፣ አስቶንቪላ ደግሞ ከሽንፈት ለማንሰራራት የሚፋለሙበት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ

ሰኞ ነሐሴ 25, 2018 144

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ምሽት በሚደረግ አንድ ጨዋታ ሲጠናቀቅ፣ የቀደመው የውድድር ዘመን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚውና የሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል ከዩሮፓ ሊግ ሻምፒዮኑ አስቶንቪላ ጋር ይጫወታሉ።

የሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል የውድድር ዓመቱን በ3 ለ 0 አሳማኝ ድል በጠንካራ ሁኔታ ሲጀምር፣ በአንፃሩ አስቶንቪላ ባልተጠበቀ የ4 ለ 0 ከባድ ሽንፈት የዓመቱን ጉዞ በመጀመሩ ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ትልቅ ትርጉም አለው።

ምሽት 4 ሰዓት ላይ በቪላ ፓርክ ስታዲየም የሚጀምረው ይህ ፍልሚያ፣ እስካሁን ሦስት ክለቦች ብቻ ሙሉ ስድስት ነጥብ ባሳኩበት ፕሪሚየር ሊግ፣ ሻምፒዮኑ አርሰናል ከደረጃ ሰንጠረዡ መሪዎች ጋር የሚኖረውን ቆይታ የመወሰን አቅም ያለው በመሆኑ በከፍተኛ ጉጉት ይጠበቃል።

የ28 ዓመቱን እንግሊዛዊ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች በቅርቡ ለዛሬ ተጋጣሚያቸው አርሰናል በዝውውር መስኮቱ አሳልፈው የሰጡት አስቶንቪላዎች፣ ወደ ሊጉ ከተመለሱበት የ2019 የውድድር ዘመን በኋላ በሜዳቸው አርሰናልን ካስተናገዱባቸው 7 ጨዋታዎች በአራቱ ድል ማድረግ ችለዋል።

ሆኖም ከ2021 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አስቶንቪላ ከእረፍት በፊት በተቆጠሩ አራት ግቦች በመክፈቻ ጨዋታ የተሸነፈው።

ይህን መጥፎ ጅማሮ በአስቸኳይ መቀየር እና ወደፉክክሩ መመለስ በአሰልጣኝ  ቡድን ትከሻ ላይ የተቀመጠ ትልቅ የቤት ሥራ ነው።

 

በሌላ በኩል የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በዚህ ጨዋታ በእግር ኳስ ሕይወቱ አዲስ ታሪካዊ ክብረ ወሰን የሚያስመዘግብ ሲሆን፣ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ 250 ጨዋታዎችን በማድረግ 10ኛው አሰልጣኝ የሚሆንበት አጋጣሚ ይሆናል።

ሁለቱም ክለቦች በዝውውር መስኮቱ በርካታ ለውጦችን እያስተናገዱ ይገኛሉ። የዩሮፓ ሊግ ሻምፒዮኑ አስቶንቪላ በዚያ መድረክ ሻምፒዮን ካደረጉት ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አብዛኞቹን ማለትም ኦሊ ዋትኪንስ፣ ሞርጋን ሮጀርስ፣ ዩሪ ቴሌማንስ፣ ሉካስ ዲኜ፣ ኤዘሪ ኮንሳ እና ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝን የመሰሉ ኮከቦች ክለቡን ለቀዋል አልያም ለመልቀቅ ጫፍ ላይ ደርሰዋል።

በተመሳሳይ መልኩ አርሰናልም እንደ ጋብሬል ጄሱስ እና ጋብሬል ማርቲኔሊ ያሉ ለዓመታት አብረውት የቆዩትን ተጫዋቾች በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀናት አሳልፎ እየሰጠ ይገኛል።

ይህ የ2ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማጠናቀቂያ ጨዋታ የሻምፒዮኑን አርሰናል በአሸናፊነት የመቀጠል ውጥን ብሎም የአስቶንቪላን ወደ ፉክክሩ የመመለስ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ምሽት 4፡00 ይጀምራል።

 

በእድሪስ አህመድ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: