17 ሺህ ኢትዮጵያውያን ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል መግባታቸውን የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ገልጿል፡፡
ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የዓይን ብሌን ልገሳ እንዲደረግላቸው ተመዝግበው ተራቸውን እየጠበቁ እንደሚገኙም የዓይን ባንኩ ጠቅሷል።
ከተመሰረተ 21 ዓመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ እስካሁን ለ3 ሺህ 600 ሰዎች የዓይን ብሌን ንቅለ ተካላ ማድረጉን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አምሳለ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
የሕክምና አገልግሎቱን በሚፈለገው ደረጃ መስጠት ያልተቻለባቸው የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ዶ/ር አምሳለ ጌታቸው ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ካባ መዝናኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል፡፡
በዚህም የለጋሾች ግንዛቤ አነስተኛ መሆን፣ የቴክኒሻኖች እና የቀዶ ሕክምና ባለሞያዎ እጥረት እንዲሁም በለጋሾች እና ድጋፍን በሚፈልጉ ሰዎች መካከል ያለው የቁጥር ልዩን ከፍተኛ መሆን ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጠው ተቋሙ ማህበረሰቡን በማንቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ብቻ ለ51 በዓይን ብሌን ጠባሳ ለሚሰቃዩ ሕመምተኞችን የዓይን ብርሃናቸውን መልሰናል ብለዋል፡፡
የዓይን ብሌን ልገሳ የሚካሄደው አንድ ሰው ሕይወቱ ካለፈ እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፣ ግለሰቡ በሕይወት እያለ የዓይን ብሌሉን ለመለገስ ቃል የገባ እና ይሄንንም ለቤተሰቡ ያሳወቀ መሆን ይኖርበታል፡፡
የዓይን ብሌናቸውን መለገስ ወይም ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ የሚፈልጉ ሰዎች በስልክ ቁጥር 0922726247 ደውለው አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አምሳለ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
በዘነቡ አደም