Search

የቱሪዝም ሕዳሴ፡- ወንጪ እና ጎርጎራ

ሰኞ ጳጉሜን 02, 2018 92

ተፈጥሮ በለገሰቻቸው አስደናቂ ውበት እና ታሪካዊ ጸጋ ተከብበው ለዘመናት በበቂ ሁኔታ ሳይለሙ የኖሩት የወንጪ እና የጎርጎራ አካባቢዎች፣ ዛሬ የአዲሱ የቱሪዝም ልማት ዋና ማዕከላት ሆነዋል።

ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አማካኝነት የተገነቡት ዘመናዊ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች እነዚህን ስትራቴጂያዊ ስፍራዎች ወደ ላቀ የኢኮኖሚ እና የመዝናኛ ምንጭነት ቀይረዋቸዋል።

ከባሕር ወለል በላይ 3 ሺህ 380 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የወንጪ ሐይቅ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ውጤት ሲሆን፣ ተፈጥሯዊ ውበቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን አትርፎለታል።

.. 2021 በዓለም የቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ መመረጡ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።

በሌላ በኩል ከታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ 61 ኪሎ ሜትር ርቀት በጣና ሐይቅ ዳርቻ የምትገኘው ጎርጎራ፣ ጥንታዊ ታሪኳን ከዘመናዊ የኢኮ ሪዞርት ልማት ጋር አዋህዳ ለዓለም አቀፍ እና ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ተመራጭ መዳረሻ ለመሆን በቅታለች።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ማራኪ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆናቸው ባለፈ ለአካባቢው እና ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

በቱሪዝም፣ በእንግዳ ተቀባይነት፣ በባህላዊ ምርቶች ንግድ እና በትራንስፖርት ዘርፍ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ካርታ ላይ ያላት ስም ከፍ ብሎ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ የሚቻልበት አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ተከፍቷል።

የወንጪ እና የጎርጎራ ልማት ትልቁ ስኬት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከቀያቸው ሳያፈናቅል የልማቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እና ባለቤት ማድረጉ ነው።

ማኅበረሰቡ በራሱ ቀዬ በተገነባው ዘመናዊ ልማት ተጠቃሚ በመሆኑ፣ በራስ የመተማመን እና የኩራት ስሜቱ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።

ወንጪ እና ጎርጎራ እምቅ የተፈጥሮ እና የታሪክ ሀብትን አውጥቶ በመጠቀም ረገድ ኢትዮጵያ የጀመረችውን አዲስ የልማት ምዕራፍ በጉልህ የሚያሳዩ ናቸው።

በመሆኑም እነዚህ ፕሮጀክቶች ሀገራችን በቱሪዝም ዘርፍ እያረጋገጠች ያለውን ሁለንተናዊ ማንሰራራት እና የከፍታ ጉዞ በግልጽ የሚያስመሰክሩ ህያው ማሳያዎች ናቸው።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: