ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፍ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ምኅዳር በስፋት ለመቀላቀል ከወሰደቻቸው ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች መካከል የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምስረታ እና ትግበራ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም በይፋ ሥራ የጀመረው ይህ የሀገራችን የመጀመሪያው ነፃ የንግድ ቀጣና፣ የንግድ እንቅስቃሴውን ለማፋጠን፣ የወጪና የገቢ ንግድን ለማቃለል እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ታልሞ የተገነባ የኢኮኖሚያችን ሞተር ነው።
በ150 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ማዕከል፣ ድሬዳዋ ከጅቡቲ ወደብ ያላትን የጂኦግራፊያዊ ቅርበትና የሎጂስቲክስ አቅም በሚገባ የተጠቀመ ነው።
ቀጣናው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን፣ የድሬዳዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን እና የደረቅ ወደብ አገልግሎትን በአንድ ማዕከል በማስተሳሰር ጠንካራ የሎጂስቲክስ ሰንሰለት መፍጠር ችሏል።
ቀደም ሲል የነበረውን የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ዘርፈ ብዙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በማሸጋገር፣ አሠራሩ ምርት ማምረትን፣ ንግድን እና ሎጂስቲክስን እንዲያካትት ተደርጓል።
በዚህም ተፈላጊ ምርቶችን ማከማቸት፣ እሴት መጨመር፣ መልሶ ማቀናጀት እና ወደ ሌሎች የውጭ ገበያዎች የመላክ ሂደቶች በአንድ ግቢ ውስጥ በቅልጥፍና እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ለዚህ እንቅስቃሴ ስኬት በነፃ የንግድ ቀጣናው ለሸቀጦች ማከማቻ የሚሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ መጋዘኖች፣ የዲጂታል መከታተያ ሥርዓቶች እና የጉምሩክ ፍተሻ ቴክኖሎጂዎች ተተክለዋል።
ባለሀብቶች የንግድ ፈቃድ፣ የጉምሩክ ሥርዓት፣ የቪዛ እና የታክስ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በፍጥነት የሚያገኙበት የአንድ መስኮት አገልግሎትም በስኬት እየተተገበረ ነው።
መንግሥት የገቢ ግብርና ምርቶች የቀረጥ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ በማድረግ፣ በነፃ የንግድ ቀጣናው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ እና ከሌሎች ታክሶች ነፃ የመሆን አሠራርን ዘርግቷል።
ይህ እርምጃ ቀደም ሲል በጅቡቲ ወደብ እና በማዕከላዊ የሀገራችን ክፍሎች መካከል ይባክን የነበረውን የትራንዚት ጊዜ እና የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቅ ተጨማሪ የማከማቻ ወጪ በከፍተኛ መጠን ቀንስዋል።
ዕቃዎች ከወደብ ወጥተው በቀጥታ ወደ ነፃ ንግድ ቀጣናው እንዲገቡ በመደረጉም የንግድ ልውውጥ ፍጥነቱ እጥፍ አድጓል።
በዚህ ምቹ አሠራር ሳቢያ ማዕከሉ በሎጂስቲክስ፣ በወጪ እና ገቢ ንግድ እንዲሁም እሴት በሚጨምሩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ ችሏል።
በተለይም ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ እና ከተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ ገበያዎች ጋር ያለውን የንግድ ትስስር በማጠናከር፣ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት ትኩረታቸውን ወደ ድሬዳዋ እንዲያደርጉ በር ከፍቷል።
የቀጣናው መነቃቃት ለአካባቢው ነዋሪዎች እና ለወጣቶች በሺዎች የሚቆጠሩ የቀጥታ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ከፍተኛ ማኅበራዊ ፋይዳ እያስገኘ ነው።
ከዚህም ባሻገር በዘመናዊ የሎጂስቲክስ አሠራር፣ በወደብ አስተዳደር እና በዓለም አቀፍ ንግድ ዙሪያ ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚገኝበት ትልቅ መድረክ ሆኗል።
በቀጣይም የቀጣናውን የቆዳ ስፋት በማሳደግ፣ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል የታገዘ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ማድረግና የፋይናንስ አገልግሎቶችን ይበልጥ ማዘመን ትኩረት የተሰጣቸው የወደፊት ግቦች ናቸው።
ድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ስምምነት የምታገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማስፋት እንደ ዋና ስትራቴጂካዊ በር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት ለምታደርገው ጉዞ ጠንካራ መሠረት የጣሉ ናቸው።
የሥራ ዕድል ፈጠራው፣ የኢንቨስትመንት ስበቱ እና የሎጂስቲክስ ማሻሻያው እንደሚያሳዩት፣ ቀጣናው የወደፊት የሀገራችን እና የምስራቅ አፍሪካ የንግድና የኢኮኖሚ ማዕከል የመሆን ሙሉ አቅም እንዳለው በተግባር ያረጋገጠ ስትራቴጂካዊ ስኬት ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: