ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ ለማፋጠን ከተቀረፁት ታላላቅ አጀንዳዎች መካከል “የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ይህ ንቅናቄ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን አቅም ለማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ለማጎልበት እና የምርት ገበያ ድርሻን ለማስፋት ያለመ ብሔራዊ ጥረት ነው።
በዚህ ሰፊ ጥረት ውስጥ በሀገራችን የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና አዳዲስ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ዋና የለውጡና የስኬቱ ሞተሮች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።
ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ በፓርኮች ውስጥ የሚሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ቁጥር ከፍተኛ እድገት አሳይቷል።
በተለይም ቀደም ሲል በኢንዱስትሪ ፓርኮች የነበረውን የውጭ ኢንቨስተሮች የበላይነት በመቀየር፣ በርካታ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው እንዲያመርቱ ሰፊ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይህንንም በተጨባጭ ለማሳየት በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ብቻ ከ750 ሚሊዮን ዶላር በላይ የመነሻ ካፒታል ያስመዘገቡ 166 አዳዲስ ባለሀብቶችን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ወደሚያስተዳድራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች መሳብ ተችሏል።
ከእነዚህ ውስጥ 84 በመቶ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸው የንቅናቄውን ስኬት ያጎላዋል።
በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ በተደረጉ የተቀናጁ ጥረቶች የአምራች ኢንዱስትሪው ዕድገት ከ4.8 በመቶ ወደ 10.7 በመቶ ከፍ ብሏል።
የንቅናቄው አንዱ እና ዋና ዓላማ በሙሉ አቅማቸው የማያመርቱ ፋብሪካዎችን ችግር መፍታት በመሆኑ፣ በግብዓት፣ በኃይል አቅርቦት እና በፋይናንስ የነበሩ ማነቆዎች ተፈትተዋል።
በዚህም የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከ44 በመቶ ወደ 70 በመቶ ማደግ ችሏል፡፡ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በጥሬ ዕቃ ችግር ተዘግተው የነበሩ በርካታ ፋብሪካዎችም ወደ ሥራ ተመልሰዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ረገድም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ሸቀጦች ታምርተው ለገበያ ቀርበዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አምራች ኩባንያዎች በፓርኮቹ ውስጥ መስፈራቸው የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ሽግግርን አፋጥኗል።
ንቅናቄው ለወጪ ንግዱም አዲስ ህይወት ዘርቷል። በብረታ ብረት፣ በኢንጂነሪንግ፣ በሀይቴክ፣ በኤሮስፔስ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በአልባሳት፣ በቆዳ ውጤቶች እና በምግብ ዘርፎች የተሰማሩ አምራቾች ምርቶቻቸውን በስፋት በማቅረባቸው የኤክስፖርት መጠን ጨምሯል።
ከባህላዊ የገበያ መዳረሻዎች ባለፈ አዳዲስ የዓለም አቀፍ ገበያዎች ላይ የ“Made in Ethiopia” ምርቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስችሏል።
በ2018 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ የኢንዱስትሪ ምርቶች 607 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ዞኖች እና ፓርኮች ውስጥ ከተመረቱት ብቻ 267 ሚሊየን ዶላር ገደማ ተገኝቷል። ይህም የጠቅላላ ዘርፉን አፈጻጸም 44 በመቶ ይሸፍናል።
በማስፋፊያ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ 433 ሺህ አካባቢ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች የተፈጠሩ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 16 በመቶው በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተመዘገበ ነው።
ንቅናቄው ለአምራች ዘርፉ እንቅፋት የሆኑ አሠራሮችን በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ካውንስል በኩል በመፍታት ምቹ የፖሊሲ ከባቢን ፈጥሯል።
አሁን ላይ የተጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ደግሞ ይህንን ዘርፍ ይበልጥ በማነቃቃት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን በማሳለጥ ለምርታማነት እድገት ተጨማሪ አቅም እየፈጠረ ይገኛል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ፓርኮቹ ከወደብ እና ከምድር ባቡር መስመሮች ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከር የሎጂስቲክስ ወጪ እና ጊዜን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች ተፋጥነዋል።
የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከነበረበት ደካማ አፈጻጸም ወደ አመርቂ ደረጃ አሸጋግሮታል።
የውስጥ አቅምን በማጠናከር፣ የወጪ ንግድን በማሳደግ እና ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የተመዘገቡት ስኬቶች የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን እውን ለማድረግ ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።
ይህ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢኮኖሚ እድገታችን ዋና መሪ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: