የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የማህበራዊ ትስስር ጥንካሬ እና የዘመናዊነት ደረጃ የሚለካው በመሬት ላይ በሚዘረጉ ጠንካራና ዘላቂ የመሠረተ ልማት አውታሮች ጭምር ነው።
የመንገድ መረብ ለሀገር ኢኮኖሚ እንደ ደም ሥር በመቆጠሩ ያለ መንገድ የተቀናጀ እድገትንም ሆነ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል አይታሰብም።
የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመላክተው በታዳጊ ሀገራት የገጠር መንገድ ሽፋን በ10 በመቶ ባደገ ቁጥር የገጠር ድህነት በ0.6 በመቶ የመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ እድል ደግሞ በ20 በመቶ የማደግ አቅም አለው።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) ማዕቀፍ መሠረትም የተቀናጀ የመንገድ መረብ መዘርጋት የእናቶችና የሕፃናት ሞትን በ35 በመቶ የመቀነስ እና የትምህርት ተደራሽነትን በ25 በመቶ የማሳደግ ታላቅ አቅም እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል።
ይህንን ዓለም አቀፋዊ እውነት መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያ በመንገድ ዘርፍ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የጻፈች ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም የነበረውን የ126 ሺህ 773 ኪሎሜትር የመንገድ መረብ፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ53 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶችን በማንጠፍ በ2018 ዓ.ም አጋማሽ ወደ 180 ሺህ 232 ኪሎ ሜትር ማሳደግ ችላለች።
ይህ አገራዊ እመርታ የትራንስፖርት አውታሩን ወደ 245 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ ለተያዘው ታላቅ አገራዊ ግብ ጠንካራ መነሻ የሆነ ሲሆን፣ ለዚህ ስኬት የመንግሥት የበጀት ትኩረት ከ2010 ዓ.ም ከነበረበት ከ30 ቢሊየን ብር በታች ተነስቶ በ2019 ዓ.ም ወደ 121 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በማደግ ከአራት እጥፍ በላይ ጭማሪ በማሳየት የካፒታል በጀት የ21 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ እንዲይዝ አድርጎታል።
ይህ የመንገድ መሠረተ ልማት እመርታ የኮንክሪትና የአስፋልት ዝርጋታ ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ ሀገር የመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን የመጨመር እና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን የማረጋገጥ ትልቅ አገራዊ ምሰሶ ነው።
ይህ አገራዊ ስኬት አህጉራዊ አድማስን ያቀፈ ሲሆን፣ በአፍሪካ ያለውን የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ወጪ በመቀነስ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) ስምምነትን በውጤታማነት ለማስፈጸም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
እንደ ላሙ ፖርት-ደቡብ ሱዳን-ኢትዮጵያ ያሉ የኮሪደር ልማቶች እና የጋራ ድንበር መቆጣጠሪያዎች በመሬት የተከበቡ ሀገራት የባሕር በር እንዲያገኙ እና እንደ IGAD፣ COMESA እና EAC ያሉ ቀጠናዊ ማህበረሰቦች በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ እንዲቀራረቡ በማድረግ የኢትዮጵያን አህጉራዊ መሪነትና አዲሱን የልማት ከፍታ በተግባር አረጋግጧል።
ሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: