በሚቀጥሉት 11 ቀናት በመካከለኛው፣ በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገልጿል።
ከባለፉት የክረምት ወራት ጀምሮ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ባገኙት በእነዚህ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ቀናትም ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠንና ስርጭት የሚኖር መሆኑን በኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
ይህ ሁኔታ በተለይ የጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ተጽዕኖ እንዳያደርስ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር አሳምነው አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ምስራቅ እና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በሜሮን ንብረት
#ኢቢሲዶትስትሪም #ሚቲዎሮሎጂ #የአየርሁኔታ