Search

በከሰል ጭስ ጉዳት ለደረሰበት ሰው የሚደረጉ የመጀመሪያ እርዳታዎች ምንድን ናቸው?

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 66

ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ካለው የአየር ፀባይ ጋር ተያይዞ ቅዝቃዜን ለመከላከል ወይም ምግብ ለማብሰል በርካቶች ከሰልን ይጠቀማሉ።

ይሁንና ከሰል በአግባቡ ካልተያዘ ወደ መርዝነት በመቀየር ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡

የከሰል ጭስ በውስጡ ካርበን ሞኖክሳይድ የሚባል በአይን የማይታይ ሽታ አልባ መርዛማ ጋዝ መያዙን ዶክተር ግርማ ዲልታታ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡

 

ይህ መርዛማ አየር ወደ ሰውነት ውስጥ ሲገባ አንጎልን፤ ልብ ላይ እንዲሁም የነርቭ ክፍሎች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

በከሰል ጭስ ወይም በቦሞኖክሳይድ ቀላል የሆነ ጉዳት የደረሰበት ሰው ማዞር፣ ግራ መጋባት፣ ሚዛን ለመጠበቅ መቸገር፣ የሆድ ህመም እና ማቅለሽለሽ፣ ለመተንፈስ መቸገር እና የመሳሰሉት ምልክቶች እንደሚስተዋሉበት ተናግረዋል፡፡

በካርቦሞኖክሳይድ በከፍተኛ ሁኔታ የተመረዘ ሰው ደግሞ መንቀጥቀጥ፣ የልብ ምት መዛባት፣ ደረት አካበባቢ የሚሰማ ከፍተኛ የልብ ምት፣ እራስን መሳት፣ ፓራላይዝ መሆን እንዲሁም እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት ሊያጋጥመው እንደሚችል ባለሙያው አስረድተዋል።

 

በከሰል ጭስ ጉዳት የደረሰበት ሰው ወደ ሕክምና ተቋም ከመወሰዱ በፊት የሚደረግለት የሕክምና እርዳታ ምን መምሰል አለበት?

 

የመጀመሪያው በከሰል ጭስ ጉዳት የደረሰበትን ሰው ክፍት የሆነ እና አየር የሚያገኝበት ቦታ ላይ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው ይላሉ ባለሙያው።

እራሱን የሳተ ሰው ከሆነ ወደ አፉ ውስጥ ምንም አይነት ነገር አለመጨመር ይመከራል፤ እንዲሁም አፉ ውስጥ ምግብ ወይም የመሳሰሉት ነገሮች ካሉ ማውጣት እንደሚገባ ባለሙያው ተናግረዋል።

እራሱን ያልሳተ ሰው ከሆነ በፍጥነት ወተት እንዲጠጣ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

ለመተንፈስ በመቸገር ላይ ያለ ሰው ከሆነ ወደ ጤና ተቋም እስኪደርስ ድረስ ደረቱን በማይጎዳ ሁኔታ በየሰከንዱ ልዩነት ጫን ጫን በማድረግ እርዳታ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡

በተለይ እያስመለሰው ያለ ሰው ከሆነ ከጭንቅላቱ ደገፍ በማድረግ በጎን እግሩን አጥፎ በማስተኛት ወደ ሕክምና ተቋም በፍጥነት መውሰድ እንደሚገባ ባለሙያው ገልፀዋል፡፡

ከሰል በምንጠቀምበት ወቅት ቤት ውስጥ በቂ አየር እንዲገባ በር እና መስኮቶች ክፍት መሆን እንደሚገባቸው አንስተው፤ ከሰልን ከተጠቀሙ በኋላም በማጥፋት ቤት ውስጥ በቂ አየር እንዲገባ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተለይ መጪው የበዓል ወቅት እንደመሆኑ ማህበረሰቡ ለእራሱም ሆነ ለጎረቤቶቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ አደጋዎችን መከላከል እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: