በዓባይ ወንዝ እና በቀይ ባህር ዙሪያ የሚስተዋለው የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ እና የብሔራዊ ደህንነት የጥቂት አሥርት ዓመታት አጋጣሚ ሳይሆን፣ የዘመናት ታሪካዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች ውጤት መሆኑ ይታወቃል።
ካይሮ በየመድረኩ የምታሰማው "የህልውና ስጋት አለብኝ" የሚለው ትርክት፣ ከጀርባው የቅኝ ግዛት ዘመን የነጠላ ጥቅም የበላይነትን የመጠበቅ እና የቀጠናውን የኃይል ሚዛን በብቸኝነት የመቆጣጠር ፍላጎት የተሸፈነበት ዲፕሎማሲያዊ ከለላ እንደሆነ ግልጽ ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል።
ግብጽ ለዘመናት የዓባይን ውኃ በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎቷን ስታስፈጽም የኖረችው በ1929 (እ.ኤ.አ) በብሪታንያ አዘጋጅነትና በ1959 (እ.ኤ.አ) በግብጽና በሱዳን መካከል በተደረጉት የሁለትዮሽ ውሎች ላይ ተመስርታ ነው።
እነዚህ ውሎች የላይኞቹን የተፋሰሱን ሀገራት በተለይም ከ85% በላይ የሚሆነውን የውኃ መጠን የምታመነጨውን ኢትዮጵያን ያገለሉ፣ ፍጹም ፍትሃዊ ያልሆኑና የቅኝ ግዛት ውርሶች ናቸው።
ካይሮ "የዓባይ ውኃ የሕልውናዬ ጉዳይ ነው" የሚለውን መፈክር የምትጠቀመው የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ ለማስገኘት እና በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሥነ-ልቦና የበላይነት ለመጫን እንደሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ አይጠፋውም። ነገር ግን፣ ከሳይንሳዊና ጂኦሎጂካዊ እውነታዎች አንጻር ግብጽ በርካታ አማራጮች ያሏት ሀገር ናት።
በምስራቃዊ ሰሃራ ስር የሚገኘውና ግብጽ፣ ሊቢያ፣ ሱዳንና ቻድን የሚያገናኘው ግዙፉ የኑቢያን አሸዋማ ድንጋይ ከርሰ-ምድር ውኃ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ የንጹህ ውኃ ክማችቶች አንዱ ነው።
ግብጽ ይህን ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብት በስፋት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አውጥታ ከመጠቀም ይልቅ፣ ሙሉ በሙሉ በዓባይ ወንዝ ላይ ጥገኛ የመሆንና የወንዙን ምንጭ የመቆጣጠር ስትራቴጂን መርጣለች።
በተጨማሪም በሰሜን በኩል ሰፊ የሜዲትራኒያን፣ በምስራቅ ደግሞ የቀይ ባህር ዳርቻ ስላላት ዘመናዊ የውኃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለኢንዱስትሪ እና ለከተሞች መጠጥ ውኃ ማቅረብ የምትችልበት ሰፊ እድል አላት።
ሆኖም ስትራቴጂካዊ ትኩረቷን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ማድረጓ የፖለቲካ የበላይነት ፍላጎቷን ያሳያል።
የካይሮ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን አልምታ እንዳትጠቀም፣ የህዝብ ቁጥሯን የሚያመዝን ኢኮኖሚ እንዳትገነባና የቴክኖሎጂና የሃይል ምንጭ እንዳትሆን የተከተሉት ዋነኛ መንገድ "ኢትዮጵያን በውስጥ ቀውስና በግጭት አዙሪት ውስጥ ማጥመድ" ነው።
ይህ ስትራቴጂ ከገማል አብደልናስር፣ ከአንዋር ሳዳትና ከሆስኒ ሙባረክ ዘመን ጀምሮ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ቋሚ የደህንነት ዶክትሪን ነው።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን (በ1875 እና 1876 እ.ኤ.አ) የግብጽ ኬዲቭ እስማኤል ፓሻ የካዲቭ ጦርን በመላክ የኢትዮጵያን የወንዝ ምንጮች በቀጥታ በኃይል ለመቆጣጠር ያደረገው ሙከራ በጉንደትና በጉራዕ ጦርነቶች በኢትዮጵያውያን ወታደራዊ ጀግንነት ሙሉ በሙሉ ከንቱ ሆኗል።
የቀጥታ ጦርነት ውድቀትን የተረዱት የካይሮ ስትራቴጂስቶች፣ አካሄዳቸውን ወደ ተዘዋዋሪ ጦርነት በመቀየር በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሱ ማናቸውንም አማጺያን፣ ተገንጣይ ቡድኖችን እና የፖለቲካ ቅሬታዎችን በገንዘብ፣ በትጥቅ፣ በዲፕሎማሲና በመገናኛ ብዙሃን ሲደግፉ ቆይተዋል።
በኤርትራ ነጻነት ግንባር (ጀብሃና ሻዕቢያ)፣ በህወሓት የ17 ዓመት የትግል ዘመን እንዲሁም በተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች ምስረታና እድገት ውስጥ የግብጽ እጅ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።
ዓላማውም የኢትዮጵያ የሰው፣ የፋይናንስና የእውቀት ሀብት ወደ ልማትና ውሃ መሰረተ-ልማቶች እንዳይዞር ማድረግ ነው።
ኢትዮጵያ በጸናች ቁጥር የዓባይ ፍሰት ከቁጥጥራቸው ውጪ እንደሚሆን ስለሚያውቁ፣ "ደካማና በችግር የተወጠረች ኢትዮጵያ" ለካይሮ ስትራቴጂካዊ እፎይታን ትሰጣለች ብለው ያምናሉ።
ይህ የካይሮ የዘመናት ሴራና የፖለቲካ ተጽዕኖ ፍፁም ተስፋ የቆረጠበትና የታሪክ አቅጣጫ የተቀየረበት አጋጣሚ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን ነው።
ግድቡ የውኃ ተፈጥሯዊ ፍሰት ሳይጎዳ ለቀጠናው ሀገራት የሚተርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ አህጉራዊ የመብራት ቋት በመሆኑ፣ ግብጽ ለዘመናት ስታስፈራራበት የነበረውን "በኃይል የመግታት" እና "በዲፕሎማሲ የማግለል" ፍላጎት ዋጋ አሳጥቶታል።
የግብጽ ስትራቴጂ በዓባይ ወንዝ ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህርና ከአፍሪካ ቀንድ የባህር መውጫዎች በማራቅ የውስጥ ደሴት አድርጎ የማስቀረት ፍላጎትንም ያካተተ ነው።
ሆኖም ካይሮ አሁንም ድረስ በቆየችበት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብና በውስጥ ተላላኪዎች አማካኝነት የኢትዮጵያን ሰላም ለመንሳት የምታደርገው ጥረት ከመሬት ላይ ያለውን እውነታ የመቀየር አቅም የለውም።
#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ ያላት ኢትዮጵያ፣ የዓባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ጠብቆ የመልማት ጉዞውን እንደቀጠለ ሁሉ፣ የታሪካዊ ገዢነቷንና የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን በማረጋገጥ በልማትና በዲፕሎማሲው መስክ የጀመረችውን የማይቀለበስ ጉዞ አጠናክራ ትቀጥላለች።
#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: