ቁማር ዓይነቱን እና መልኩን እየቀያየረ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ አሁን ያለንበት ዘመን ላይ ደርሷል።
ዓለማችን አሁን ላይ በቴክኖሎጂ ራሷን በመዘወር የተለያዩ ፈጠራዎችን በመፍጠር ሀገራት ከሀገራት ጋር በፉክክር ላይ ይገኛሉ።
ቴክኖሎጂ የራሱ የሆነ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ በሌላው መልኩ አጠቃቀሙ ልክ ካልሆነ ትውልድ ወደ ማይሆን መንገድ እንዲያመራ ያደርጋል።
ዘመን ካመጣቸው ቴክኖሎጂዎች አንዱ ታዲያ የ‘ቨርቹዋል' ቁማር ሲሆን፣ ብዙ ወጣቶች እና ጎልማሳዎች በዚህ ሱስ ተጠምደው መውጣት የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደደረሱ ይነገራል።
የፍካት ሥነ-ልቦና ማማከር አገልግሎት መሥራች እና የሥነ-ልቦና ባለሙያ የሆኑት ኤርሚያስ ኪሮስ፣ ‘ቨርቹዋል’ ቁማር ከሌሎች ቁማር እና ሱሶች የተለየ አይደለም ይላሉ።
ባለሙያው ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፣ አንድ ግለሰብ በአደንዛዥ እፅ ምክንያት የሚፈጠሩበት ተፅዕኖዎች በቁማርም በተመሳሳይ ይፈጠሩበታል።
በቨርቹዋል ቁማር (ውርርድ) የተጠመዱ ሰዎች ከራሳቸውም ሆነ ከማኅበረሰቡ ጋር እንደማይግባቡ፤ በቁማሩ ምክንያትም እንቅልፍ ማጣት እና ወደ ሌላ ሱሶች ለመግባት እንደሚገደዱ አንሥተዋል።
በዚሁ የቁማር ሱስ ገንዘብ እና ንብረታቸውን አጥተው የከሰሩ፣ ቤተሰባቸውን የበተኑ ከዚያም አልፎ ራሳቸውን ያጠፉም እንዳሉ ተናግረዋል።
ይህ ‘ቨርቹዋል' ቁማር ብዙ ወጣቶች ትምህርታቸውን ትተው መዋያቸው እያደረጉ በሆኑ ትልቅ የትውልድ ፈተና እየሆነ ነው ብለዋል።
ሀገር ተረካቢው ትውልድ እየጠፋበት እና ለአዕምሮ ቀውስም እየተጋለጠበት የሚገኘው ይህ ቁማር፣ ሀገር ዜጎቾን እያጣችበት እና እየከሰረች ትገኛለች ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ቁማርተኞች ሦስት ዓይነት የአስተሳሰቡ መዛባቶች እንደሚያጋጥማቸው ይነገራል።
የመጀመሪያው ሲያሸነንፉ በችሎታቸው እንደሆነ ያስባሉ፤ ሲሸነፉ ደግሞ በዕድል መሆኑን በማሳብ ቁማሩን የሚተውበት ምክንያት እንዳይኖር ያደርጋሉ።
ሌላኛው መርጦ ማስታወስ ሲሆን የሆነ ጊዜ እንደአጋጣሚ በድንገት ያሸነፉበትን ጊዜ በማስታወስ ለመጫወት ይገፋፋሉ።
"ሌላኛው ዞሮ ዞሮ ብሬን አስመልሳለው" የሚል እሳቤ በመኖሩ በተደጋጋሚ እንዲጫወቱት ያደርጋቸዋል።
የአዕምሮ ጤናን የሚያሳጣው ይህ ቁማር በራስ መተማመንን እንደሚሸረሽር እና በራስ ተስፋ ለመቁረጥ እንደሚዳርግም ባለሙያው አብራርተዋል።
ሕክምና እና ክትትል እንዲሁም የራስ ተነሳሽነት ካለ መሻሻል እንደሚችል ገልጸው፣ ይህ ዝምተኛ ገዳይ ሁሉም ሊያወግዘው እና በቃ ሊለውም ይገባል ሲሉ መክረዋል።
በሜሮን ንብረት