በሦስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ታላቁ የፋርስ ፈላስፋ ማኒ፣ በዘመኑ ከነበሩት አራት ግዙፍ የዓለም ኃያላን መንግሥታት (ሮም፣ ፋርስ፣ ቻይና እና አክሱም) አንዷ አክሱም መሆኗን የመሰከረው በዘፈቀደ አልነበረም።
ይህ ታሪካዊ እውነታ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድ እና የባሕር ኃይል መስመር ላይ የነበራትን የገዛችበትን እና የደመቀችበትን ወርቃማ ዘመን የሚያሳይ ነው።
በወቅቱ የአዶሊስ ወደብ የአክሱም ሥልጣኔ የዓለም አቀፍ ንግድ መግቢያ እና መውጫ በር በመሆን አገልግሏል። የኢትዮጵያ የንግድ መርከቦች እና ነጋዴዎች ቀይ ባሕርን አቋርጠው ከሮማውያን፣ ከዓረብ ምድር፣ ከፋርስ እና ከሕንድ ጋር ይነግዱ ነበር።
የአክሱም ሳንቲሞች በንግድ ማዕከልነት በመላው የሜዲተራኒያን እና የሕንድ ውቅያኖስ ቀጣናዎች ይሰራጩ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን ፍጹም የበላይነት እና የሥልጣኔ መሪነት የሚያረጋግጥ የታሪክ ሕያው ምስክር ነው።
የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ታሪካዊ ትሥሥር በሒደት በርካታ የጂኦፖለቲካዊ አውሎ ነፋሶችን አስተናግዷል። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኦቶማን ቱርክ ድንበር ተሻጋሪ መስፋፋት በቀይ ባሕር ዳርቻዎች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የስዊዝ ካናል መከፈት እና ተከተሎ የመጣው የአውሮፓ ኃያላን ሀገራት አፍሪካን የመቀራመት ሩጫ የአፍሪካ ቀንድን የፖለቲካ ካርታ መልክ ቀየረው።
ኢትዮጵያ በ1896 (እ.አ.አ) በታላቁ የዓድዋ ድል የቅኝ ገዥዎችን ወረራ መክታ ነፃነቷን እና ታሪካዊ ክብሯን ባስጠበቀችበት ወቅትም ቢሆን፣ በቀይ ባሕር ዳርቻዎች ላይ የተፈጠረው የቅኝ ግዛት መዋቅር ሀገራችንን ከቀጥታ የባሕር በር መዳረሻዋ ለመነጠል መሠረት ጥሏል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ኤርትራ በ1952 (እ.አ.አ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ መሠረት ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ተዋሃደች። ይሁን እንጂ የፌዴሬሽኑ መፍረስ፣ የተከተለው የሦስት ዐሥርታት መራራ ጦርነት እና በ1993 (እ.አ.አ) የኤርትራ ነፃ ሀገር ሆኖ መውጣት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቋ ቀጥተኛ የባሕር መዳረሻ የሌላት (Landlocked) ሀገር አድርጓታል።
በአሁኑ ወቅት ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና በአፍሪካ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወጪ እና ገቢ ንግዷን በጎረቤት ሀገራት ወደቦች በተለይም በጂቡቲ በኩል ታከናውናለች። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ እና ለሎጂስቲክስ አገልግሎት ብቻ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ታወጣለች።
ይህ ሁኔታ የገቢ እና ወጪ ንግድ ምርቶችን ተወዳዳሪነት ይጎዳል፤ የአቅርቦት ሰንሰለት ስጋቶችን ይፈጥራል፤ ከዚህም ባሻገር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ጥንካሬን እና የሕዝቧን ፈጣን ዕድገት የሚመጥን ተለዋዋጭነት እንዳይኖራት ገደብ ይጥላል።
በመሆኑም የባሕር መዳረሻ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ከታሪካዊ ትዝታ እና ከሥልጣኔ ዐሻራነት ባለፈ፣ የአሁኑ እና የመጪው ትውልድ ሕልውና፣ የብሔራዊ ደኅንነት እና የዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ ስትራቴጂያዊ መሠረት ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ ፍላጎት እና ጥያቄ በኃይል ወይም በግጭት ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ሕጎች፣ በዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች እና በመደመር የጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ላይ የተመሠረተ ነው።
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ የንፁህ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የቴሌኮም እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ትሥሥር ከጎረቤቶቿ የወደብ ሀብት ጋር በማጣመር የጋራ ዕድገት እና ብልጽግና የማምጣት ራዕይ አላት።
ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው፦ የየሀገራቱን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ሙሉ በሙሉ በማክበር፤ በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ (UNCLOS) እና አህጉራዊ ስምምነቶች ማዕቀፍ ውስጥ በመንቀሳቀስ፤ እንዲሁም የቀጣናውን ሀገራት ኢኮኖሚ በማስተሣሠር የጋራ የንግድ እና የልማት ማዕከል በመፍጠር ነው።
ከጥንቱ የአዶሊስ የንግድ ማዕከልነት እስከ ዘመናዊው የቀጣናዊ ጂኦፖለቲካ እውነታ ድረስ፣ የቀይ ባሕር ጉዳይ የኢትዮጵያ የታሪክ፣ የባህል እና የኢኮኖሚ ደም ሥር ነው።
ታሪካዊ ትሥሥሯን በሚገባ በመረዳት፣ ሰላማዊ እና ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ መንገድ በመከተል እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ የልማት አጋርነት በመፍጠር ኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ አቅሟን በማስፋፋት የቀጣዩን ዘመን የብልጽግና ጉዞዋን እውን ታደርጋለች።
በኢንትሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: