Search

"የሰብዓዊ ክብር መጠበቅ የፈጣሪን ሥራ ማክበር ነው"፦ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

ረቡዕ ጥቅምት 11, 2019 71

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከጀርመን ኤምባሲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አባል የሃይማኖት ተቋማት በሰብዓዊ ክብር፣ በሰላም ግንባታ፣ በየእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከር እንዲሁም የሐሰት መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን በመከላከል ረገድ ያላቸውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ እና ተቋማዊ አቋም ይፋ አድርገዋል።

ፈጣሪ ሰውን ክቡር አድርጎ የፈጠረው በመሆኑ የሰውን ሰብዓዊ ክብር መጠበቅ የፈጣሪን ሥራ ማክበር እንደሆነ በመግለጫው ተመላክቷል።

ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት እና ተከታዮች ለራሳቸው እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ለሌላው ማድረግ እንዳለባቸው የሚያስተምሩ በመሆናቸው፣ የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም የአምልኮ ስፍራዎች እና የሃይማኖት ነፃነት ማክበር፣ መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ አባቶች  ጥሪ ቀርቧል።

ከሃይማኖት አስተምህሮ የተቃረኑ የማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን ለመግታት የሃይማኖት ተቋማት ምእመኖቻቸውን በስፋት ማስተማር፣ መገሠጽ እና መከላከል እንዳለባቸውም በመግለጫው ተገልጿል።

ሴቶችን እና ወጣቶችን በሰላም ግንባታ ሥራዎች ላይ በስፋት ማሳተፍ ሰላምን ለማጽናት፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን ለማጠናከር እና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቅሷል።

ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ከሃይማኖት አስተምህሮዎች ጋር በማቀናጀት ግጭቶችን በውይይት እና በዕርቅ መፍታት እንደሚገባ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያዘጋጀው ይህ መድረክ አባል ተቋማቱ ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝቦች አብሮነት እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ያንጸባረቁበት ነው። 

በመድረኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል እና የኢትዮጵያ 7ኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ተወካዮች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

በላሉ ኢታላ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: