Search

የመደመር መንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ የፖሊሲ ነፃነት እና የተከበረው አገራዊ የመፈጸም አቅም

ረቡዕ ጥቅምት 11, 2019 71

የመደመር መንግሥት የጀመራቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የክትትል፣ የበጀትና የጥናት ክፍተቶችን በመቅረፍ የኢትዮጵያን የመፈጸም አቅም፣ የፖሊሲ ነፃነት እና የበላይነት በተግባር ያረጋገጡ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪው አለቃው ከበደ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ቀደም ሲል የነበሩ በርካታ ፕሮጀክቶች ያልተሳኩት በቂ ጥናት ባለመደረጉ፣ የበጀት እና የክትትል ክፍተቶች በመኖራቸው ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን ከእነዚያ ተሞክሮዎች ትምህርት በመውሰድ በተከናወኑ ተግባራት መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ችግሮችን የሚያቃልሉ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

አለቃው ከበደ (ዶ/ር) አክለው እንደገለጹት እነዚህ ፕሮጀክቶች "ኢትዮጵያ በራስ አቅም ግዙፍ ስራዎችን መስራት አትችልም" የሚለውን የተሳሳተ እሳቤ በመስበር በቂ የፕሮጀክት መፈጸም አቅም እንዳላትና "እንችላለን" የሚል አዎንታዊ የስነ ልቦና ግንባታ እንድታመጣ አስችለዋል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቶቹ በራስ አቅም መከናወናቸው የፖሊሲ ነፃነትን የሚያጎናጽፉ ገጠርና ከተማን በማስተሳሰር አካታችነትን የሚያረጋግጡ እንዲሁም በቀጣናዊ ትስስርና በትልቁ ኤርፖርት ግንባታ እቅድ አማካኝነት የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኙ ናቸው ብለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪና መምህር የሆኑት ዱጋሳ አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ምርትን በመጨመር የገቢ ንግድን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እሴት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ዱጋሳ አበበ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት እና በግብርና ዘርፎች የሚታየው የምርት መስፋፋት የዶላር ፍላጎትን ከመቀነሱ ባለፈ የለውጡ አመራር፣ የመንግሥትና የሕዝብ መተባበር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አቅም እያሳደገ ይገኛል።

ይህም ከምግብና ከገንዘብ በላይ የሀገርን ውበት፣ ዝና፣ ክብር እንዲሁም የቴክኖሎጂና የሰራተኛ እጅን የማድነቅ ባህልን ያመጣ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በመደመር መንግሥት እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር፣ በከፍተኛ የሥራ ዲሲፕሊንና በጥብቅ የጊዜ ገደብ የሚመሩ በመሆናቸው፤ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉና ለትውልድ የሚሻገሩ ታሪካዊ ሀገራዊ ቅርሶች ሆነው ይመዘገባሉ።

ይህ አገራዊ የመፈጸም አቅም እና የፖሊሲ ነፃነት ኢትዮጵያ በራሷ ብቃትና ሀብት የቆመች #ትልቅሀገር፣ በሥራና በቴክኖሎጂ የተራመደ #ትልቅሕዝብ እንዲሁም ለቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ከፍታ የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: