ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ ከኢቲቪ (ETV) ጋር ባደረጉት ሰፊ ማብራሪያ ላይ ያነሷቸው ነጥቦች ለዘመናት ታፍኖ የነበረውን የትግራይ ሕዝብ እውነተኛ ብሶትና እውነት ያንጸባረቁ ናቸው ሲሉ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢቢሲ (EBC) የሰጡት የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የህገወጡ ህወሓት ቡድን ላለፉት 50 ዓመታት ክልሉን እንደ ግል ድርጅቱ በመቁጠር የሕዝቡን ሀብትና መብት ለራሱ ጥቅም ሲያውል ቆይቷል።
ቡድኑ የሕዝቡን ባህልና ስነ-ልቦና የማይወክሉ ጎጂ አስተሳሰቦችን ሲጭን መቆየቱን የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በዚህም ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ለረጅም ዘመናት በረሃብ፣ በስደትና በመከራ ውስጥ እንዲኖር መደረጉን ገልጸዋል።
የቡድኑ አመራሮች የራሳቸውን ልጆች በአውሮፓና በአሜሪካ በጥሩ ሁኔታ እያስተማሩና ከሕዝብ የዘረፉትን ሀብት እያፈሰሱባቸው ይገኛሉ ያሉት ነዋሪዎቹ፣ በአንጻሩ ግን የትግራይን ወጣት ለጦርነትና ለጥፋት እንደ ማገዶ ሲጠቀሙበት መቆየታቸውን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል አብዛኛው ወጣት በጦርነት የተጎዳና ክልሉ ከፍተኛ የሰውና የቁሳቁስ ኪሳራ ማስተናገዱን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ቀደም ሲል የቀረቡ የሰላም ጥሪዎችን ህገ ወጡ ህወሓት ባለመቀበሉ የተከሰተው ጥፋት ዳግም መደገም እንደሌለበት አሳስበዋል።
የመቐለ ከተማ ነዋሪዎችና ወጣቶች አሁን የተፈጠረውን የሰላም እድል በመጠቀም ከፌዴራል መንግሥትና ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በወንድማማችነት ለመኖር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ሕዝቡ የሚፈልገው ሰላምን፣ ልማትንና ከረሃብ ነፃ መሆንን በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፉና ወደ ልማት ሥራዎች ለመመለስ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ሰላም ለማስፈን እያደረጉት ያለውን ጥረት ያመሰገኑት ነዋሪዎቹ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት በሙሉ የሕዝቡን የሰላምና የልማት ፍላጎት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ የመቐለ ነዋሪዎች ድምፅና የሰላም ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመች #ትልቅሀገር፣ ወንድማማችነትን ያጠናከረ #ትልቅሕዝብ እና ለትግራይ ክልል አዲስ የተስፋ ንጋትን የፈነጠቀ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ ለትግራይ ህዝብም የቀጣዩ ዘመን የብልጽግናና የሰላም ምዕራፍ መሆኑን ያበስራል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: