ፉክክሩ በሜዳ ላይ ያሉት የሃያ ሁለቱ ተጫዋቾች ፉክክር ብቻ አልነበረም። አዲስ አበባ ስታዲየም ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቷል።
ከ9 ሰዓቱ ጨዋታ 2 ሰዓት አስቀድሞ ሜዳው ጠጠር መጣያ አልነበረውም። ሜዳ ላይ የኳሱን የበላይነት ለመውሰድ ተጫዋቾች ይፋለማሉ። ደጋፊዎች ደግሞ የዜማ ፉክክሩን ተያይዘውታል።
የቃላዊ ሥነ ጽሑፍ ስንኞች ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ፣ ከትሪቡን ወደ ካታንጋ፣ ከካታንጋ ወደ ትሪቡን ይወረወራሉ። እንግዳ ሆነው በስታዲየሙ የታደሙ ሁሉ በትርዒቱ መደመማቸውን በፈገግታ እየገለጹ ነው።
በዚህ ሂደት ላይ እያሉ አንድ ዜማ፣ ከየትኛው የስታዲየሙ ክፍል አካባቢ እንደተጀመረ ያልታወቀ ዜማ ስታዲየሙን ናጠው። የአዲስ አበባ ውበቶች፣ የስታዲየሙ ድምቀቶች፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሀብቶች የሆኑት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በአንድነት ዘመሩ። የሁላቸውም አልፋ እና ኦሜጋ ኢትዮጵያ ናትና ከውስጥ ፈንቅሎ የወጣ ዝማሬን አቀነቀኑ።
አንጋፋው ድምፃዊ ማሕሙድ አሕመድ ስለ ኢትዮጵያ ያዜመው ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃ!
'ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣ በአባቶቻችን ደም'
አባቶቻችን ኢትዮጵያን በደማቸው አቆይተዋታል። በጀግንነት ተፋልመው ሀገርን አጽንተዋል። ኢትዮጵያን አስከብረዋል። በደም እና በአጥንት የቆየች ሀገር - ኢትዮጵያ!
'እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም፣ የደፈረሽ ይውደም'
ኢትዮጵያ እናታችን ነች። እናት በሌላ አትተካም። ሀገራችን ኢትዮጵያ አቃፊያችን ነች። ታሪኳ የሚያኮራን፣ መውደዳችን ጥልቅ የሆነ ሊገለጽ የማይችል ፍቅር። ድምፃዊው እንዲህ አለ፤ 'እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም! የደፈረሽ ይውደም'!
ኢትዮጵያን ማንም ይነካት ዘንድ የሚቻለው የለም። ሰይፈ ነበልባል ነች። የነኳትን የምታቃጥል፣ አስጠባቂ ልጆቿም ይላሉ፤ የደፈረሽ ይውደም፣ ይጥፋ። ድምፃዊ ማሕሙድ ይቀጥላል፦
'ለበጎ ከሆነ ለቁም ነገር ጉዳይ
ጎረቤት ወዳድ ነን እንግዳ ተቀባይ'
እነዚህ ስንኞች የኢትዮጵያውያንን ዕሴቶች ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የኢትዮጵያውያን ባህል እንግዳ ተቀባይነት፣ ሰው አክባሪነትና መውደድ፣ እንዲሁም ጽኑ ፍቅር ነው።
ኢትዮጵያውያን ጎረቤትን መውደድ ከጥንት እስከ ዛሬ ያለ እና የነበረ ባሕርያችን ነው። ኢትዮጵያም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ቅድሚያ ለጎረቤት ነው የምትለው። የሚወዷትን ትወዳለች፣ የሚያከብሯትን ታከብራለች።
ደራሲው ቀጠለና እነዚህን ስንኞች ደረደረ፦
'ግን ሀገራችንን ክፉ እሚያስባትን
ቆራጥ ነን ልጆቿ አንወድም ጥቃትን'
ኢትዮጵያ የሚወዷትን ትወዳለች። ፍቅሯም የላቀ ነው። ቅድሚያ ለጎረቤት በሚል መርሕ ትንቀሳቀሳለች። ግን የነኳትን አትምርም።
"የአበው የአርበኝነት ቅርስ፣ የነፃነት የድል ፋና
ወደ ትውልድ ተሸጋግሮ፣ ወርሶት ጸንቷል እንደገና"
የሚሉት ዜጎቿ ኢትዮጵያን በክፉ የሚያስባትን አይምሩም።
"የማንጨበጥ ነበልባል፣ እሳት ነን ለጠላታችን
ፍሙ ከርቀት ይፋጃል፣ ብረት ያቀልጣል ክንዳችን"
የሚለውን መዝሙር እዚህ ላይ ማምጣት ያስፈልጋል። ልጆቿ በእርሷ አንደራደርም። ቆራጥነታችን እስከ ቀራንዮ ነው፤ እስከ መስዋዕትነት ድረስ።
ደጋፊዎች ታዲያ በስታዲየም ውስጥ ሆነው ይህንን ፍቅር ነው የገለጹት። ሜዳ ላይ የቡናና የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ፉክክር በኳሱ የበላይነት ለመውሰድ ብቻ ነው። አንድ በሚያደርጋቸው በኢትዮጵያ ጉዳይ ግን በአንድነት አዜሙ፤ በኅብረት ዘመሩ። ኢትዮጵያ እናታቸው ነችና ፍቅራቸውን ያለ ስስት ገለጹ።
በሀብታሙ ካሴ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: