የዓለም አቀፍ የሕብረት ሥራ ማህበራት ጥምረት የአፍሪካ ቅርንጫፍ (ICA-Africa) አህጉራዊ ጉባኤውን በኢትዮጵያ ማካሄድ ጀምሯል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው ይህ ጉባኤ “ለሁሉም የሚገባ ሥራ፤ የሠራተኛ ሕብረት ሥራ ማህበራት እና የእንክብካቤ ኢኮኖሚ በአፍሪካ ውስጥ ማካተትን ማሳደግ” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄድ ሲሆን፣ የሕብረት ሥራ ማህበራት ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት እና ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክቱትን የጎላ አስተዋጽኦ ለማጠናከር ያለመ አህጉራዊ መድረክ ነው።
የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽነር ጌትነት ታደሰ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሕብረት ሥራ ማህበራት የኢኮኖሚ ተቋማትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ለተሻለ ውጤታማነት ማህበራቱ የካፒታል፣ የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የአሠራር መመሪያዎች እና የገበያ ትሥሥር በቀጥታ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸት ይገባል ብለዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራን ዕውን ለማድረግ እና አህጉራዊ አጀንዳዎችን ለማስቀጠል ከመንግሥታት፣ ከኢጋድ፣ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከሌሎች አጋሮች ጋር ያለው ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።
የዓለም ሕብረት ሥራ ማህበራት ጥምረት ፕሬዚዳንት ማክላውድ ማሎንዛ በበኩላቸው፣ ጉባኤው የሕብረት ሥራ ማህበራት ሠራተኞች ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶችን እንዲያደራጁ፣ የሙያ ክህሎትን እንዲያዳብሩና የተሻለ የድርድር አቋም እንዲኖራቸው የሚያስችል ንቅናቄ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የአይሲኤ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት መስፍን ገ/ስላሴ ማህበራቱ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የተሻለና ፍትሃዊ የሥራ ሁኔታን ለመፍጠር፣ የሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎን ከፍ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
በተለይም ወጣቶች እና ሴቶች ሥራ ለማግኘት የሚገጥሟቸውን እንቅፋቶች ለማስወገድ እና አገልግሎቶችን ለማጠናከር ትኩረት መሰጠት እንዳለበት በመድረኩ ተነስቷል።
ይህ አህጉራዊ ጉባኤ ከዓለም አቀፉ የሁለተኛው የዘላቂ ልማት ግቦች፣ ከአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 እና ከአፍሪካ የዲሰንት ሥራ አጀንዳ ማዕቀፎች ጋር የተጣጣመ ነው።
መድረኩ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያጎለበተችውን ልምድ ለሌሎች ሀገራት የምታካፍልበት እና አህጉራዊ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ የምታሸጋግርበት መሆኑም ተመላክቷል።
በብሩክታዊት አስራት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: