Search

አዲስ አበባ የ2026 የዓለም ከተሞች ቀን “የሸንሃይ አዋርድ” ሽልማት አሸነፈች

ቅዳሜ ጥቅምት 21, 2019 119

አዲስ አበባ በተባበሩት መንግሥታት UN-Habitat በቻይና ያዘጋጀውን የፈረንጆቹ 2026 የዓለም ከተሞች ቀን “የሸንሃይ አዋርድ” ሽልማት ማሸነፏን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ! መልዕክት ይህ ድል ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ኢትዮጵያ ታላቅ ኩራት ነው ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሰዎች ሰፈራ ፕሮግራም (UN-Habitat) እና በቻይና የተዘጋጀውን የሸንሃይ ሽልማት፣ በዘላቂ፣ አካታች፣ ሰው ተኮርና አይበገሬ የከተማ ልማት ውጤታማ ሥራዎችን ላከናወኑ በየዓመቱ ለአምስት ከተሞች የሚሰጥ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም አዲስ አበባ በ2026 ከተሸላሚ ከተሞች አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህ ለከተማችን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አይደለም በማለት በ2024 በUN-Habitat እና በደቡብ ኮሪያዋ ሴዑል ከተማ የተዘጋጀው “የሴዑል ከተማ ሽልማት”አሸናፊ መሆኗን አስታውሰዋል።

እነዚህ ተከታታይ ዕውቅናዎች በከተማ ልማት የተከናወኑ ሥራዎችንና የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያመለክታሉ ያሉት ከንቲባዋ፣ የሸንሃይ ሽልማቱ በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑት የከተማ ልማት ሥራዎች ውጤታማነት፣ ዘላቂነትና ለነዋሪዎች ያላቸው ጠቀሜታ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘታቸውን ያሳያል ብለዋል።

ለዚህ ስኬት ካበቋት ዋና ዋና የልማት አቅጣጫዎች መካከል፦

•  ሰው ተኮር አቀራረብን ከከተማ መልሶ ማልማት ጋር በማቀናጀት የነዋሪዎችን ፍላጎት ቅድሚያ መስጠት፤

•  የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሻሻል የተከናወኑ ሥራዎች፤

•  በከተማ ኮሪደሮችና በወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች አካታችና የተቀናጀ ልማትን ማረጋገጥ፤

•  የትራንስፖርት አገልግሎትንና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች፤

•  አረንጓዴነትን፣ ጽዳትንና የከተማ ውበትን በማሻሻል ምቹና ለኑሮ ተስማሚ አካባቢ መፍጠር ይገኙበታልም ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

እነዚህ ተግባራት የከተማዋን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር፣ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት በማሳደግና አዲስ አበባን ተወዳዳሪ ከተማ በማድረግ ረገድ ያላቸውን አስተዋጽኦ ያሳያሉ።

በተለይም በታዳጊ ሀገራት ከባድ ፈተና የሆነውን የከተማ መልሶ ማልማት በስኬት ማከናወን እንደሚቻል ያሳየችው ተሞክሮ፣ ለሌሎች ከተሞችም ተግባራዊ ትምህርት የሚሰጥ ምሳሌ ሆኗል ሲሉም አክለዋል።

ይህ ድል የተግባር ስኬት፣ የጋራ ጥረትና የጋራ ውጤት ነውና  ሁላችንም በድጋሚ እንኳን ደስ አለን በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: