ሺሕ ዘመናትን ያስቆጠረ የአስተዳደር ታሪክ ያላት እና ለዓለም የዲፕሎማሲ እንዲሁም የሥልጣኔ እሴቶችን ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ ለገጠሟት ሁለገብ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመስጠት እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቷን ለማጠናከር የመደመር ፍልስፍናን እንደ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ማዕቀፍ በመጠቀም ላይ ትገኛለች።
ጠንካራ እና ጽኑ ሀገር ለመገንባት ሐሳብን፣ ሰውን፣ ሀብትን እና ተቋማትን በማቀናጀት ከቀደምት ስህተቶች መማር ግዴታ ነው።
የለውጥ ጉዞዎች ሁልጊዜም ከቁጭት የሚነሱ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ሀገር ወደኋላ ስትቀር እና ዓለም ወደፊት ሲራመድ የሚፈጠር ቁጭት ለትክክለኛ ለውጥ ዋና መነሻ ነው።
ይሁን እንጂ ቁጭት መነሻ እንጂ መዳረሻ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም፤ የጉዞው መዳረሻ ጠንካራ ሥርዓት፣ ማጠቃለያው ደግሞ ዘላቂ ሥልጣኔ ነው።
ጠንካራ ሥርዓት በአንድ ጀምበር የሚገነባ ሳይሆን ትዕግሥትን፣ ስክነትን፣ ጥበብን እና ተከታታይ ጥረትን የሚጠይቅ ውስብስብ ሂደት ነው።
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተሳስረው፣ ተዋልደው እና ተጋምደው፣ ችግሮቻቸውን በውይይት እና በዕርቅ ፈተው ኖረዋል። ዳር ድንበራቸውን በደም እና በአጥንታቸው ያስከበሩት ክፉ እና ደጉን ዘመን በአብሮነት ያሳለፉት በመደመር እሳቤ በመጋመዳቸው ነው።
ባለፉት ዘመናት የነበሩ አካሄዶች ከሚያዋጣው የሀገር ውስጥ መንገድ ይልቅ አቋራጭ በመምረጥ ከባሕር ማዶ የተቀዱ ርዕዮተ ዓለሞችን በግድ መሬት ላይ ለመትከል ሲሞክሩ ቆይተዋል።
መሬቱን ለዘሩ ወይም ዘሩን ለመሬቱ ማስተካከል ባለመቻሉ አዝመራው አረም እያበቀለ ኢትዮጵያ ለከፋ ችግር ስትዳረግ ኖራለች።
ከሥሩ የተነጠለ ዛፍ እና ከምንጩ የተቆረጠ ወንዝ እንደሚደርቅ ሁሉ ሀገራዊ መሠረቱን ጥሎ የሚጀመር የሥልጣኔ ጉዞም ሩቅ ሊሄድ አይችልም።
በመሆኑም የመደመር እሳቤ የበለጸገች አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት እንደ ሀገራዊ የማሰቢያ ቋንቋ ያገለግላል። ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ጥናቶች እና ፍተሻዎች ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የታሪክ እና የጥበብ ሀብት እንዳላት የተረጋገጠ ሲሆን ይህም የመደመር እሳቤ ዋና መሠረት ሆኖ አገልግሏል።
ኢትዮጵያውያን በታሪክ ዘመናት ሁሉ ብዝኃነትን ከአንድነት፣ የእምነት ልዩነትን ከእሴት ትስስር፣ የግል ፍላጎትን ደግሞ ከጋራ ጥቅም ጋር ደምረው በመጓዝ አብሮነታቸውን አስጠብቀዋል።
አውሮፓውያን እና እስያውያን የራሳቸውን ባሕል እና ፍልስፍና መሠረት አድርገው ሥልጣኔያቸውን እንደገነቡት ሁሉ፤ ኢትዮጵያም ያላትን የሥልጣኔ ሀብት በማዘመን በሀገር በቀል እሳቤ ላይ የታነጸ ጠንካራ ሥልጣኔ መገንባት እንደምትችል በተግባር አሳይታለች።
በታሪኳ ለዓለም ያበረከተችው የመንግሥት አስተዳደር እና የነፃነት ተምሳሌትነት ዛሬ ላይ የገጠሟትን የዴሞክራሲ፣ የሰላም እና የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በመደመር እሳቤ ያለፉትን ጉድለቶች እያረመች ወደፊት በጋራ ለመጓዝ የሚያስችል ሁለገብ መንገድ በመከተል ላይ ትገኛለች።
በዚህም አሰራር ኢትዮጵያ የመደመር እሳቤን በተግባር በመተርጎም ታሪካዊ አሸናፊነቷን አስጠብቃ የብልጽግና ጉዞዋን እያረጋገጠች፣ የብዝኃነት ውብ እሴቶቿን በማጠናከርም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ከፍ እያደረገች ትገኛለች።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: