Search

ሁለቱ ዲሲፕሊኖች፦ ዒላማውን በብቃት የሚመታ፣ ዓላማውንም በጽናት የሚያሳካ የመደመር ትውልድ

ቅዳሜ ጥቅምት 21, 2019 96

ወታደሮች የሚያነጣጥሩበት ዒላማ አላቸው፤ ሲቪሎች ደግሞ የሚኖሩለት ዓላማ አላቸው። የሁለቱም የመጨረሻ ግብ ግን አንድ ነው፤ እሱም ድልን ማስመዝገብ! ታዲያ አንድ የሲቪል መሪ ከወታደራዊ ካምፕ ምን ይማራል? ወታደራዊ ዒላማን ከሀገራዊ ዓላማ ጋር ማዋሃድስ ማለት ምን ማለት ነው?

“ወርቅ በእሳት ይፈተናል፣ ሰውም በፈተና ይጠራል” እንዲሉ፣ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለመገንባት እና ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ፣ ባሕላዊ እና ሞራላዊ እሴቶች የተሸመኑበትን ሁለንተናዊ ብልጽግና ዕውን ለማድረግ በዕውቀት የተሳለ ብቻ ሳይሆን በዲሲፕሊን የታነጸ አመራር የግድ ይላል።

ሀገር ለመሪዎቿ የምትሰጠው አደራ ከባድ ነው፤ ይህንን አደራ ለመሸከም ደግሞ በአካል የዳበረ፣ በሞራል የጠነከረ፣ በጥበብ የበሰለ እና በሕዝብ ተቆርቋሪነት መንፈስ የሚነሣሣ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያስፈልጋል።

ለዚህም ነው የመደመር መንግሥት አመራሮች በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ገብተው ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙት።

ወታደራዊ ሳይንስ እና ሕይወት የሰውን ልጅ ውጫዊ እና ውስጣዊ ማንነት በመቅረጽ፣ በአካልም ሆነ በመንፈስ የመርሕ ሰው እንዲሆን በማስቻል ለዘመናት ታላላቅ መሪዎችን ያፈራ ተወዳዳሪ የሌለው ትምህርት ቤት ነው።

ከዚህ ወታደራዊ ልምድ የሚቀሰሙት እሴቶች ለሲቪል አስተዳደር እና ለመደመር ሥልጣኔ ስትራቴጂ ወሳኝ አቅም ይፈጥራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ከላይ እስከ ታች በአንድ ሰዋሰው መግባባት እና መናበብ፣ የተሰጠን ግዳጅ እና ለሕዝብ የተገባን ቃል ያለምንም ማመካኘት አከናውኖ መጨረስ፣ ወትሮ ዝግጁነት፣ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት እንዲሁም ሥነ ምኅዳርን በሚገባ ተጠቅሞ የጋራ ግብን በጋራ ማሳካት ከወታደራዊ ዲሲፕሊን የሚገኙ ታላላቅ ትሩፋቶች ናቸው።

“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው መዋቅሩ ከታች እስከ ላይ በአንድ የሥራ ዲሲፕሊን ሲናበብ ለምንም እና ለማንም የማትበገር ጽኑ ሀገር መገንባት እና የሀገርን ደኅንነት ምንጊዜም ማረጋገጥ ይቻላል።

የሁርሶው ሥልጠና ዋና ምስጢርም ይኸው ነው፤ ወታደራዊውን የአፈጻጸም ዲሲፕሊን ከሲቪሉ የልማት እና የዴሞክራሲ ዓላማ ጋር ማጋባት።

ሁለቱን ዲሲፕሊኖች በማገናዘብ ዒላማውን በብቃት የሚመታ፣ ዓላማውንም በጽናት የሚያሳካ እና ተተኪ የሚያፈራ ትውልድ እየተገነባ ይገኛል።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: