በዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ መልክዓ-ምድር ውስጥ የባህር በር ባለቤት መሆን የሉዓላዊነትና የኢኮኖሚ ነፃነት ማዕከል ነው።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እያስተዳደረች በዓለም ቀዳሚዋ የባህር በር የሌላት ሀገር መሆኗ የተፈጥሮና የታሪክ አለመመጣጠን መሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የድንበር ማሻሻያ አጀንዳ ሳይሆን ከጥንታዊው አክሱም ግዛት ከአዱሊስ ወደብ እስከ ዘመናዊው ታሪክ ድረስ የነበራትን ሕጋዊ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት መልሶ የማረጋገጥ አገራዊ ትግል ነው።
በ1983 ዓ.ም የተፈጠረው የባህር በር መቋረጥ የጊዜያዊ ታሪካዊ አደጋ እንጂ የረጅም ጊዜ ህልውና እውነታ አለመሆኑን የመደመር መንግሥት በተደጋጋሚ አጽንኦት ሰጥቶበታል።
ከኢኮኖሚ ማክሮ እይታ አንፃር ሲታይ የባህር በር አለመኖር ለታዳጊዋ የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ እጅግ ከባድ ኪሳራን አስከትሏል።
ኢትዮጵያ ከምታካሂደው አጠቃላይ የውጭ ንግድ ውስጥ እስከ 95 በመቶ የሚሆነውን በጎረቤት ጅቡቲ በኩል የምታስተላልፍ ሲሆን በየዓመቱ ለወደብ አገልግሎት እና ለትራንስፖርት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማውጣቷ የውጭ ምንዛሪ ክምችቷን በእጅጉ ፈትኖታል።
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚተነትኑት አንዲት ግዙፍ ሀገር በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለወደብ ክፍያ ማውጣቷ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ የሚጣል የማይታይ ግብር ነው።
በመሆኑም ቀጥተኛ አስተማማኝ እና ዘላቂ የባህር በር ማግኘት ለድህነት ቅነሳ እና ለኢኮኖሚ ነፃነት ወሳኝ ቅድመ-ሁኔታ ነው።
በአለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ ስንመለከተው የባህር ሕግጋት ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን (UNCLOS) ክፍል 10 አንቀጽ 125 የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ወደ ባህር የማግኘት እና የመተላለፍ መብት እንዳላቸው በግልጽ ይደነግጋል።
ዓለም አቀፍ የሕግ ሊቃውንት እንደሚስማሙበት የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ከባህር ጋር ያላቸውን ተደራሽነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በቂ ሕጋዊ ከለላ ሊኖራቸው እንጂ እንደ "ሕጋዊ ወላጆች አልባ" (Legal Orphans) መታየት የለባቸውም።
የባህር ዳርቻ ሀገራት ሉዓላዊነት እና የባህር በር የሌላቸው ሕዝቦች ፍትሃዊ የባህር ተደራሽነት መብት በአለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ማዕቀፎች መስተካከል አለበት።
የቀይ ባሕር ደኅንነት ከባህር ዳርቻ ሀገራት ፍላጎት ብቻ በላይ የሰፋ ነው። የባብ-ኤል-መንዴብ (Bab-el-Mandeb) ሰርጥ እና የቀይ ባሕር ኮሪደር የዓለምን 12 በመቶ የባህር ንግድ 30 በመቶ የኮንቴይነር ማጓጓዣ እና እስከ 15 በመቶ የነዳጅ ንግድ የሚሸፍን በመሆኑ ለአለም አቀፍ ኢኮኖሚ የደም ስር ነው።
የኢትዮጵያን የመሰለ ግዙፍ ሕዝብ እና ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት ያለው ሀገር ከቀይ ባሕር የደኅንነት ማዕቀፍ ውጪ ማድረግ አደገኛ የሆነ የደኅንነት ክፍተት (Security Vacuum) ይፈጥራል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት በኃይል ድንበርን የመቀየር አጀንዳ ሳይሆን በግልፅ የዲፕሎማሲ ውይይቶች፣ በጋራ የባህር መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች፣ በፍትሃዊ የንግድ ተጠቃሚነት እና በአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ማዕቀፍ ውስጥ በመተግበር የቀይ ባሕርን ኮሪደር ከፉክክርና ውጥረት ማዕከል ወደ የጋራ ብልጽግና ኮሪደር የመቀየር ታሪካዊ ተልዕኮ ነው።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: