የልጅነት ትዝታዎቻችን ቀላል የደስታ እና የፈገግታ ምንጮች ብቻ አይደሉም፤ ይልቁንም ጥልቅ ማኅበራዊ እሴቶችን፣ ሀገራዊ ጥበቦችን እና የሕይወት ፍልስፍናዎችን አሟልተው የያዙ ሕያው ማስተማሪያዎቻችን ናቸው።
በተለይም በትምህርት ቤት የዕረፍት ሰዓት በደመቀ መንፈስ ከሚደረጉ ጥንታዊ ባህላዊ ጨዋታዎቻችን መካከል ‘የጠጠር ቅልልቦሽ’ ጨዋታ አንዱ እና ዋነኛው ነው።
ጨዋታው እንዲሁ ሲታይ እጅግ ቀላል ቢመስልም፣ በጥበቡ ውስጥ ግን ከፍተኛ ትኩረትን፣ ፈጣን የእጅ እና የዐይን ቅንጅትን፣ ፍጹም ትዕግሥትን እና እያንዳንዱን እርምጃ በጥንቃቄ የማቀናጀት ክህሎትን የሚጠይቅ ጥበብ ነው።
በዚህ ባህላዊ ጨዋታ ውስጥ በመጀመሪያ ጠጠሮቹ መሬት ላይ በስፋት ይበተናሉ። ተጫዋቹም አንዱን ዋና ጠጠር ወደ አየር በመወርወር፣ ሌሎቹን በተለያዩ ዙሮች አንድ በአንድ፣ ሁለት ሁለት እያለ በመጨረሻም ሁሉንም የተበተኑ ጠጠሮች በአንድ ጊዜ እና በጥንቃቄ በእጁ ለመሰብሰብ ይሞክራል።
ይህንን ስኬታማ ለማድረግ አዕምሮን፣ ዐይንን እና እጅን በአንድ ወጥ መዋቅር ማቀናጀት ግዴታ ነው። ይሁንና የዚህ የጨዋታ ሂደት ጥልቅ ምስጢር ከቀላል መዝናኛነት ባሻገር እጅግ ታላቅ ሀገራዊ ፍልስፍናን ያዘለ ነው፤ ይኸውም የተበተነውን አቅም ወደ አንድ ማዕከል የማሰባሰብ፣ ልዩ ልዩ ጥረቶች እና ችሎታዎችን በማቀናጀት የጋራ ድል የማስመዝገብ መርሕ ነው።
ይህ ጥበብ በተመሳሳይም በተለያዩ ማኅበረሰባዊ ክፍሎች፣ ልዩ ልዩ ሐሳቦች እና ሀገራዊ አቅሞች በአንድነት ሲቀናጁ አሸናፊ እና ፀንቶ የሚቆም ሀገረ መንግሥት መገንባት እንደሚቻል በግልጽ ያመላክታል።
በዚህ ረገድ የመደመር እሳቤ የተለያዩ ማኅበረሰባዊ እሴቶችን እና እምቅ አቅሞችን በማቀናጀት የጋራ ብሔራዊ ግብን ለማሳካት የሚያግዝ መሪ መርሕ ሆኖ ይገኛል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪካዊ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ሉዓላዊነቷን አጠናክራ ለማስቀጠል ከፋፋይ አተያዮችን በመሻገር የጋራ ትርክትን፣ የጋራ ኃላፊነትን እና የጋራ ዓላማን በፅናት እያጠናከረች ትገኛለች።
ዛሬ ሀገራችን በዚህ አዲስ የዕድገት አቅጣጫ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በጋራ በመምከር ለሀገራዊ ፈተናዎች የጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚያደርጉትን ታሪካዊ ጥረት አጠናክራለች።
በብሔራዊ ምክክር ሂደቱ አማካኝነት ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች፣ በሰላም ግንባታ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት፣ እንዲሁም የሀገርን ሉዓላዊነት በሚመለከቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ በነፃነት እንዲመክሩ የተደረገበት ታላቅ የዴሞክራሲ መድረክ ተፈጥሯል። ይህም ልዩነቶችን በሠለጠነ ውይይት የማስታረቅ እና ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትን የማጠናከር ተግባራዊ አቅምን አሳይቷል።
በጠጠር ጨዋታ ውስጥ የሚታየው ሌላው ድንቅ ፍልስፍና ደግሞ፣ አንዱን ዋና ጠጠር ወደ አየር እየወረወሩ ሌላውን ከመሬት ላይ ሲያነሱ፣ ቀድሞ በእጅ ላይ ያለውን ጠጠር ሳይጥሉ በጥንቃቄ ጠብቆ የመቀጠል ጥበብ ነው።
ይህም የመደመር እሳቤ ያለንን ታሪካዊ መልካም እሴት፣ ባህል እና ኩራት ሳናጣ እና ሳናፈርስ፣ አዳዲስ እና ጠቃሚ ዘመናዊ አቅሞችን በመጨመር ወደፊት የመራመድ መርሕን ያንፀባርቃል።
ነባሩን የትናንት መልካም እሴት ጠብቆ ማቆየት፣ የጎደለውን ማሟላት እና የተሻለ አዲስ አቅም በመፍጠር ሀገርን መገንባት ዘላቂ መሠረት ያለው ሂደት ነው። የመደመር እሳቤ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በተቋማት ደረጃ የተበተኑ ሀገራዊ አቅሞችን በማቀናጀት ለዓለም አቀፍ ውድድር ብቁ ያደረገ ሀገራዊ ውጤት አምጥቷል።
ይህ ፍልስፍና መሬት ወርዶ በተግባር ሲተረጎም የሀገራችንን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የቀየሩ ግዙፍ የልማት ምዕራፎች እውን ሆነዋል። በዚህ ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በርካታ ውስብስብ ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችን ተሻግሮ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ የሀገራችንን የጋራ ጥረት፣ መደመር እና የማይናወጥ ጽናት የሚያስመሰክር ታሪካዊ የታላቅነት ማረጋገጫ ሆኗል።
በተመሳሳይ መልኩ በመዲናችን አዲስ አበባ እና በሌሎች ዋና ዋና ክልል ከተሞች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞቻችንን ገጽታ ከማዘመን ባለፈ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን፣ የዜጎችን የኑሮ ጥራት እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን አዲስ ከፍታ ላይ አድርሶታል።
በተጨማሪም ከ53 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገው ብሔራዊ መታወቂያ ‘ፋይዳ’ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ ትኩረት ያገኙት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች ግንባታ የኢትዮጵያን እምቅ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ሀብት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ውጤት የቀየሩ ስኬቶች ናቸው።
በውጭ ግንኙነት እና በዲፕሎማሲው ዘርፍም ሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሟን በማስቀደም፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በሉዓላዊነት መርሆች ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የዲፕሎማሲ አቋም ይዛለች።
የፍትሐዊ የባሕር በር አጠቃቀምን ጨምሮ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የምታካሂደው ጥበብ የተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም አስተማማኝ በሆነ መንገድ የሚያስጠብቅ ነው።
የልጅነት የጠጠር ጨዋታ የሚያስተምረን ትልቅ ሀገራዊ ትምህርት አለ፤ እያንዳንዱ ጠጠር በጨዋታው ውስጥ የራሱ ወሳኝ ቦታ እንዳለው ሁሉ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋም ታላቋን ሀገር በመገንባት ሂደት ውስጥ የራሱ የማይተካ ሚና እና ታሪካዊ ኃላፊነት አለው።
የተበተኑ አቅሞችን እና እሴቶችን በአንድነት ማቀናጀት፣ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም እና በጋራ ራዕይ መቆም ለጸናች እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ መሠረቶች ናቸው።
የትናንቱን መልካም ሀገራዊ እሴቶች ሳንጥል፣ የዛሬውን እምቅ አቅም በመደመር፣ ለነገዋ የበለጸገች ኢትዮጵያ የጀመርነውን የታላቅነት ጉዞ አጠናክረን እንገፋበታለን።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: