እአአ በ1993 የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ የተፈፀመው ታሪካዊ ስህተት በአንድ ጀምበር ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ ሀገር አድርጓት አደረ።
የባሕር በርን የመሰለ መሠረታዊ የሕልውና ጉዳይ ያለምንም ሕጋዊ ሂደት አሳልፎ በመስጠት ሀገራችንን ባሕር በር አልባ ያደረገው የታሪክ ጠባሳ ግን አሁንም አልሻረም።
ይህ ቁስል እንዲሽር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኃላፊነት የተሞላበት ገንቢ ሚና ሊጫወት እንደሚገባ በዩናይትድ ኪንግደም ክዊንስ ዩኒቨርሲቲ ቤልፋስት የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪው ብዙነህ ጌታቸው (ዶ/ር) አመላክተዋል።
ዶ/ር ብዙነህ ከኢቲቪ አዲስ ዳያሎግ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የኤርትራያውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እና የድንበርና የባሕር በር ድርድር ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች መሆቸውን ገልጸዋል።
በወቅቱ ግን ምንም ዓይነት ውይይት ሳይደረግ እነዚህ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ሆን ተብሎ በአንድ እንዲደባለቁ መደረጉን አስታውሰዋል።
የአስተማማኝ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የብሔራዊ ደህንነት፣ የኢኮኖሚ ሽግግር እና በዓለም አቀፍ ገበያ የንግድ ተወዳዳሪነት ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ቀጣና አዲስ አይደለችም ያሉት ዶ/ር ብዙነህ፣ በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ታሪካዊው የዓዱሊስ ወደብ የኢትዮጵያን ተራራማ ቦታዎች ከሜዲትራንያን፣ ከዓረብ ፔኒንሱላ እና ከሕንድ ውቅያኖስ የንግድ መስመሮች ጋር ያገናኝ እንደነበረ ጠቅሰዋል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመንም ቢሆን ኢትዮጵያ በአሰብ እና በምፅዋ ወደቦች በኩል ቀጥታ የባሕር በር እንደነበራት አንስተው፤ አሁን ግን ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገራችን የባሕር በር አልባ መሆኗ ፈርጀ ብዙ ጫና ማድረሱን ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጪ እና ገቢ ንግድ በጅቡቲ ኮሪደር ላይ የተመሠረተ ነው።
ዶ/ር ብዙነህ እንዳሉት፣ በዚህ ኮሪደር ላይ የሚፈጠር ማንኛውም ያልተጠበቀ መስተጓጎል የኢትዮጵን የነዳጅ አቅርቦት እንዲሁም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ኤክስፖርት ያዛባዋል።
ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ክፍያ እንደ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ እና የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎች ያሉ መሠረታዊ ገቢ እቃዎች ዋጋ እንዲጨምር ከማድረጉ ባሻገር የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ጫና ይፈጥራል።
በአንድ መተላለፊያ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን የንግድ ድርድር አቅምን የሚገድብ ከመሆኑም በላይ፣ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በአቅርቦት መስመር ስጋት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዳያደርጉ ይገድባል።
ኢትዮጵያ ግዛት የማስፋፋት ፍላጎት አላት የሚሉ ውንጀላዎችን ውድቅ ያደረጉት ተመራማሪው፣ የሀገራችን መሻት የራሷን የባሕር በር በመጠቀም ቀጣናዊ ትስስርን፣ የኢኮኖሚ ትብብርን እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማራመድ መሆኑን አብራርተዋል።
እናም የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን (UN) ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የጋራ የውይይት መድረኮችን እንዲያመቻቹ፣ በተለይም የኤርትራ መንግሥት ወደ ውይይት ጠረጴዛ መጥቶ እንዲነጋገር ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያን ሕጋዊ የባሕር በር ጥያቄ ችላ ማለት በቀጣናው አለመረጋጋትን እንደሚያራዝም የጠቆሙት ተመራማሪው፤ ኃያላን ሀገራት በቀይ ባሕር ኮሪደር ወታደራዊ እና የንግድ መሠረታቸውን ባስፋፉበት በዚህ ወቅት፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች ሰላማዊ እና በኢኮኖሚ የዳበረች ኢትዮጵያን ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ዋና መሠረት አድርገው ሊወስዷት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: