ታዋቂው የጂኦፖለቲካ ተንታኝ ቲም ማርሻል "የጂኦግራፊ እስረኛ መሆን ድህነትን አሜን ብሎ መቀበል ነው" ሲል ያስቀመጠው እውነታ፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ፈተናና የነገ ዕጣ ፈንታ በግልጽ ያሳያል።
ውኃ የሕይወት መገኛና የ21ኛው ክፍለ ዘመን የጂኦፖለቲካ መዘውር በሆነበት ዓለም፣ የኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማት እና ቀጣይነት ከሁለት ታላላቅ የውኃ አካላት ማለትም ከዓባይ ወንዝ እና ከቀይ ባሕር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።
ብሔራዊ ጥቅምን ከዕለታዊ ፖለቲካ ባሻገር በሰከነ መንፈስ ለሚመረምር ዜጋ የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ወይም የስሜት ጉዳይ ሳይሆን ድህነትን አሜን ብሎ ላለመቀበል የሚደረግ የሀገርና የትውልድ ህልውና ትግል ነው።
ይህንን መልክዓ-ምድራዊ እስረኝነት መስበር ለምን እንዳስፈለገ የተፈጥሮ ፍትሕ፣ ታሪክና የኢኮኖሚ ስሌት ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ከከፍታ ቦታዎቿ በሚነሱት ዓባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ፣ ኦሞ እና ዋቢ ሸበሌ ወንዞች ለጎረቤቶቿ ሕይወት የምትዘራ፣ የተፈጥሮ ወንዝ ለማይደርሳት ጅቡቲም በራሷ ወጪ የመጠጥ ውኃ የምታቀርብ ሀገር ናት።
ከጎረቤቶቿ አንድም ሊትር ውኃ ሳትቀበል ይህን ሁሉ በረከት ስታካፍል እና በገዛ ገንዘቧና መሬቷ በምትገነባው ግድብ ዙሪያ ዓለም በነፃነት ሲከራከር፣ የደም ስሯ የሆነውን የቀይ ባሕር ጉዳይ በምሁራን እና በፖለቲካ ልሂቃን ደረጃ እንኳን ማንሳት እንደ ነውር ተቆጥሮ መቆየቱ ታሪካዊ ስብራት ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት አንድ ብርጭቆ ውኃን ለደቂቃ መሸከም ቀላል ቢሆንም ለሰዓታት ማቆየት እጅን እንደሚያደነዝዝ ሁሉ፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ የደረሰ እና በ2030 ወደ 150 ሚሊዮን የሚቃረብ ሕዝብ ይዞ ያለ ባሕር በር ታፍኖ መቀጠል ለከፋ የኢኮኖሚ እና የህልውና አደጋ የሚዳርግ ሸክም ነው።
ከዓለም 44 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት መካከል የኢትዮጵያን ያህል ግዙፍ ሕዝብ የተሸከመ ሀገር የለም።
የኢትዮጵያ የጥንት ሥልጣኔ ገናናነት የተገነባው ከቀይ ባሕር ጋር በነበረው ቀጥተኛ ትስስር ሲሆን ከባሕሩ በራቀችባቸው ዘመናት ግን ሀገራዊ አቅሟ ተዳክሟል።
ራስ አሉላ አባነጋ "ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ወሰን ነው" ያሉትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በጂኦግራፊ እና በኢኮኖሚ መነሻነት ተገቢ የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳላት ያሰፈረው ሰነድ ይህንኑ ታሪካዊ እና ሕጋዊ እውነታ ያጸናሉ።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የባሕር በር ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት እስከ 30 በመቶ አስተዋጽኦ ሲኖረው፣ ለወደብ ኪራይ በየዓመቱ የምናወጣው የውጭ ምንዛሪም እንደ ሕዳሴ ግድብና ማዳበሪያ ፋብሪካ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የሚገነባ ሀብት በመሆኑ፣ በጂኦግራፊ እስር መቆየት ለዘላቂ ድህነት መፈረም ነው።
ይህንን እስረኝነት የምንሰብርበት መተንፈሻ በር የሚገኘው ከጦርነት እና ከጉልበት በጸዳ፣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ አዲስ ቀጠናዊ እሳቤ ነው።
የቅኝ ግዛት ድንበሮች ከፋፈሏቸው እንጂ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በጅቡቲ እና በሶማሊያ የሚገኙ ማኅበረሰቦች አንድ ባህልና ደም ያላቸው ወንድማማቾች ናቸው።
ስለሆነም ኢትዮጵያ በአሰብ፣ ምጽዋ፣ አዱሊስ፣ ጅቡቲ ወይም ዘይላ ወደቦችን በአማራጭ መጠቀሟ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ውህደት መፍጠር ያስችላል፡፡
ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ የቀጠናው መንግሥታት ልክ በበርበራና በሞቃዲሾ ወደቦች ለሩቅ ሀገራት እንደተሰጠ የውኃና የደም ትስስር ላላት ኢትዮጵያም በር ሊከፍቱ ይገባል።
የመደመር መንግሥት የሰከነ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን አጠናክሮ ሲቀጥል የፖለቲካ ልሂቃን፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙኃን አጀንዳውን በጥናት፣ በዓለም አቀፍ ሕግና በተገራ ትርክት ማገዝ አለባቸው።
የመደመር ትውልድም ታላቁ የህዳሴ ግድብን በአንድነት እውን እንዳደረገው ሁሉ የጂኦግራፊ እስረኝነትን በእውቀት እና በሰላማዊ ዲፕሎማሲ ሰብሮ ድህነትን አሜን ብሎ እንደማይቀበል በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: