ዓሣ አማካይ መጠኑ የሽምብራ ወይም የማሽላ ፍሬ ያሚያክል እንቁላል አለው።
ይህ ከዓሣዎች የሚገኝ እንቁላል ታዲያ ደረጃቸው ከፍተኛ በሆኑ ሆቴሎች ውስጥ የሚቀርብ እና ዋጋውም እጅግ ውድ የሆነ የምግብ ዓይነት እንደሆነ ይነገርለታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል እንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሱ ለኢቢሲ "ጤናዎ በቤትዎ" ፕሮግራም እንደገለጹት፣ የዓሣ እንቁላል እንደ ዓሣዎቹ ዝርያ የተለያየ መጠን ገፅታ እና ቀለም አለው።
የዓሣ እንቁላል በጣም ውድ እና በይዘቱም ከፍተኛ ጠቃሜታ ያለው የምግብ ዓይነት መሆኑን የሚናገሩት ምሁሩ፣ በመጠን፣ በይዘት እና በጣዕማቸውም እንደሚለያዩ ገልጸዋል።
የዓሣ እንቁላሎች ሲበሉ የቅቤ፣ የለውዝ፣ እና ኾምጣጣ ጣዕም እንዳለቸውም ተናግረዋል።
የዓሣ እንቁላሎች ተፈጥሯአዊ ከሆኑ ዓሣዎች የሚገኙ፣ ሲበሉ የሚፈነዳ ነገር ያላቸው፣ ነገር ግን በጣም ደስ የሚል፣ ውድ እና የቅንጦት ዓይነት የምግብ ዓይነቶች ውስጥ የሚካተቱም አብራርተዋል።
የአንድ ‘ኪዊ’ የጫማ ቀለም መያዣ የሚያክል መጠን ዕቃ የሚታሸግ የዓሣ እንቁላል ዋጋው 2 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደሆነም ነግረውናል።
በኢትዮጵያ አንድ ሰው በዓመት የሚጠቀመው የዓሣ መጠን ከአንድ ኪሎ ግራም በታች መሆኑን ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሱ ይናገራሉ።
በአፍሪካ ደረጃ ግን እንደ አህጉር አንድ ሰው በዓመት የሚጠቀመው 10 ኪሎ ግራም ዓሣ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 20.2 ኪሎ ግራም ይደርሳል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ዓሣን ለምግብ መጠቀምን ለማሳደግ የዓሣ ማሠልጠኛ ተቋማትን ማስፋፋት፣ ለዓሣ እርባታ የተሻለ መሠረተ ልማት መዘርጋት፣ ለወጣቶች ስለ ዓሣ እርባታ ሥልጠና መስጠት፣ ሠርቶ ማሳያዎችን ማስፋፋት እና ለኅብረሰተቡ በቂ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
ለዘርፉ በቂ ትኩረት መስጠት ከተቻለ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ፣ የገቢ ማግኛ በማድረግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመምራት የውጭ ምንዛሪ ማትረፍ እንደሚቻልም ባለሙያው ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለምግብነት መዋል የሚችሉ ከ200 በላይ የዓሣ ዝርያዎች ያሏት ብትሆንም ሀብቱን ከመጠቀም አንፃር ግን ገና መሆኑን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የዓሣ ምርምር ማዕከል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በላሉ ኢታላ