ምድራችን ዛሬ ከሰደድ እሳት እስከ ፈጣን የበረዶ መቅለጥ የደረሰ ከባድ የአየር ንብረት ቀውስ ገጥሟታል።
የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ የዓለም ሙቀት መጠን ማሻቀብ እና የሙቀት አማቂ ጋዞች ክምችት ታይቶ በማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ የምድራችንን ሕልውና እየፈታተነ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ይህንን ዓለም አቀፍ አደጋ ለመመከት የበለጸጉ ሀገራት የገቡትን ቃል በፖለቲካ ቁርጠኝነት ማጣት ምክንያት ባለመፈጸማቸው የችግሩ ውስብስብነት እየጨመረ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የመደመር ፍልስፍናን መሠረት በማድረግ ለዚህ ዓለም አቀፍ ችግር ጠንካራ መፍትሔ የሚሆን ተጨባጭ ተግባራዊ እርምጃ ወስዳለች።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል እና የደን ሽፋንን በማሳደግ የችግሩ መፍትሔ ከተፈጥሮ ጋር መታረቅ እና ተፈጥሮን በማደስ መሆኑን በተግባር አሳይታለች።
በተፈጥሮ ማደሻው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደ ሐረማያ ሐይቅ ያሉ ተፈጥሯዊ የውኃ አካላት አገግመዋል፤ ወፎች ከስደት ተመልሰዋል፤ የድርቅ መጠን ቀንሷል።
የአረንጓዴ ልማቱ የብክለት ቅነሳን፣ የከተሞች ማደስን፣ የንጹሕ ኃይል አጠቃቀምን እና ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረግ ሽግግርን አካትቶ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን እያስገኘ ነው።
ከአቮካዶ እና ቡና የወጪ ንግድ ዕድገት እስከ የሥራ ዕድል ፈጠራ ድረስ ያለው እጅግ አበረታች ውጤትም የመደመር አቅም በተግባር ምን ሊሠራ እንደሚችል በግልጽ አሳይቷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በንጹሕ የኃይል ልማት የጀመረችው ጉዞ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለቀጣናዊ የኃይል ትስስር ያበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቱርክዬ አንታሊያ በተካሄደው 31ኛው የአየር ንብረት መሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፍ በካዮች ልቀታቸውን በአስቸኳይ እንዲቀንሱ ጠይቀዋል።
ዓለም አቅሙን ቢደምር ተፈጥሮን ማደስ እንደሚችል የኢትዮጵያ ተጨባጭ ልምድ ማሳያ መሆኑን በማንሳት፣ ዓለም ይህንን ተሞክሮ ቀምሮ በተደመረ አቅም ምድራችንን እንዲያድን ጥሪ አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ በመመረጧ ተጨባጭ ልምዷን ለዓለም ለማካፈል ሰፊ ዕድል አግኝታለች።
መላው ዓለም ከተለመደው የዳተኝነት አዝማሚያ ወጥቶ ቃሉን በተግባር በማሳየት እና በተደመረ አቅም ምድራችንን ከጥፋት እንዲታደግ ኢትዮጵያ ጥሪ አቅርባለች፡፡
ምላሹ ግን እንደ ከዚህ ቀደሙ የማይፈጸም ቃል ሳይሆን፣ በመደመር አቅም ምድራችንን ከተደቀነባት የሕልውና አደጋ በማዳን መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥታለች።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: