Search

ልማት በሰው ልጅ ክብር ሲለካ

ሰኞ ኅዳር 07, 2019 87

የአንድ ሀገር ዕድገት እና ብልጽግና የሚለካው ባላት የተፈጥሮ ሀብት እና በምትገነባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ብቻ አይደለም።

እነዚህ ሀብቶች እና መሠረተ ልማቶች የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት፣ ክብር እና መሠረታዊ ፍላጎት የሚመልሱ ሰው ተኮር ሲሆኑ ብቻ ሀገር በትክክለኛው የብልጽግና ጎዳና ላይ ትራመዳለች።

የመደመር መንግሥት የልማት ፍልስፍና ዋነኛ መገለጫም ግዙፍ ሀገራዊ ራዕዮችን ከዜጎች ቀጥተኛ ፍላጎት ጋር አስተሳስሮ መምራት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጉባ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በይፋ ሲመርቁ፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በ30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚተገበሩ ሰባት ግዙፍ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶችን ማብሰራቸው ይታወሳል።

እነዚህ ብሥራቶች ኢትዮጵያን በኃይል፣ በኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርትና በአቪዬሽን ዘርፍ የአፍሪካ ተምሳሌት የሚያደርጉ ናቸው።

በውስጣቸውም ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፋብሪካዎች፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የባቡር መሠረተ ልማት እንዲሁም በአፍሪካ ግዙፉን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያካትታሉ።

የጉባ ብሥራቶችን እጅግ ልዩ የሚያደርጋቸው ግን ከእነዚህ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ጎን ለጎን የዜጎችን መሠረታዊ የመኖሪያ ቤት ችግር የሚቀርፈውን የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በእኩል ስትራቴጂያዊ ክብደት አካትተው መቅረባቸው ነው።

በብዙ ሀገራት የልማት ታሪክ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የዜጎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ሂደት በጊዜ ብዛት ይመለሳል የሚል እሳቤ የተለመደ ነው።

የመደመር መንግሥት ግን የልማት ማዕከሉ ሰው በመሆኑ ከ30 ቢሊዮን ዶላሩ የልማት በጀት ውስጥ የቤት ልማቱ ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው በማድረግ፣ ግዙፍ መሠረተ ልማቶችን እና የዜጎችን መጠለያ የማግኘት መብት እኩል ሚዛን ላይ አስቀምጧቸዋል።

የጋዝ፣ የነዳጅ ማጣሪያ እና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ አቅም በማሳደግ ሉዓላዊነቷን ሲያጸኑ፣ የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ደግሞ በከተሞች ያለውን የቤት ኪራይ ጫና በማቃለል ማኅበራዊ ፍትሕን ያረጋግጣል።

በጉባ የተገባው ቃል በወረቀት ላይ ሳይቀር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር መሸጋገሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጀመረው ሰፊ የቤቶች ልማት እንቅስቃሴ በግልጽ ያሳያል።

በአሁኑ ወቅት የዚሁ ሀገራዊ መርሐ ግብር አካል የሆኑ 100 ሺህ መኖሪያ ቤቶች በመዲናዋ በ21 የተለያዩ ቦታዎች (ሳይቶች) ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነቡ ይገኛሉ።

ይህ እንቅስቃሴ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የቤት ባለቤት ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠረ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ነው።

ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምረቃ ማግስት በጉባ የተበሠሩት ሰባቱ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የብልጽግና ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ የታሪክ ድልድዮች ናቸው።

በአዲስ አበባ በተጨባጭ መሬት ላይ የወረደው የቤቶች ልማትም መንግሥት ዕድገትን የሚለካው በሕንፃዎችና በፋብሪካዎች ግዝፈት ብቻ ሳይሆን የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት በመመለስ ጭምር መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ አኩሪ ምዕራፍ ነው።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: