Search

የአረንጓዴ ምህንድስና ተምሳሌት የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 108

ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በቢሾፍቱ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው ግዙፉ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የአፍሪካን የአቪዬሽን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የዘመናዊ ምህንድስና እና የአካባቢ ጥበቃ ፍልስፍናን ድንቅ ውሕደት በይፋ እያሳየ ይገኛል።

የክፍለ ዘመኑ ግዙፍ የአቪዬሽን መሠረተ ልማት የሆነው ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የኢኮኖሚ ዕድገት እና የተፈጥሮ ጥበቃ ተጣጥመው መጓዝ እንደሚችሉ በተጨባጭ እያረጋገጠ ነው።

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ታዳሽ ኃይልን መሠረት ባደረገ አረንጓዴ ዲዛይን እየተተገበረ ይገኛል። በተርሚናሎች ግዙፍ ጣሪያዎች ላይ የሚዘረጉ ሰፋፊ የሶላር ፓነሎች እና በዙሪያው የሚቋቋሙ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ማዕከላት በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ፈጽሞ በማስቀረት ንጹህ የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባሉ።

በዓለም አቀፉ ታዋቂ ተቋም ዛሃ ሃዲድ አርክቴክትስ (ZHA) የተሠራው የሥነ-ሕንፃ ዲዛይን ሕንፃዎቹ የፀሐይ ጨረርን በቀጥታ እንዳይቀበሉ በሰሜናዊ አቅጣጫ እንዲገነቡ ተደርጓል።

በ60 ሜትር ከፍታ በሚገነባው ማዕከላዊው ሕንፃ (Central Beacon Athyrium) አማካይነት ሙቅ አየርን ወደ ላይ በመሳብ እና ከስምጥ ሸለቆ መልክዓ ምድር በተቀዳው አረንጓዴ ስፍራ በመታገዝ ኃይል ቆጣቢ የሆነ ተፈጥሯዊ የአየር ማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂ ይተገበራል።

ዘላቂ የውኃ አያያዝ ሥርዓቱ ሌላኛው የፕሮጀክቱ ጠንካራ ምሰሶ ነው። ከግዙፍ ጣሪያዎች የሚሰበሰበው የዝናብ ውኃ በመሬት ውስጥ ማጠራቀሚያዎች እንዲከማች፣ የዝናብ ውኃ ማቆያ ረግረጋማ ፓርኮች እንዲቋቋሙ እና የታጠበ ውኃ መልሶ ማጣሪያ ሥርዓቶች እንዲዘረጉ በዲዛይኑ ተካትቷል።

ይህ ዘመናዊ ዑደት የውኃ ሀብትን ከብክነት በመታደግ ለአካባቢ ጥበቃ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያሳያል።

ለዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ (SAF) ዝግጁ የሆኑ ማከማቻዎች እና ማሰራጫዎች በዲዛይኑ ውስጥ መካተታቸው ዓለም አቀፍ የካርቦን ልቀት ቅነሳ ደንቦችን ሙሉ በሙሉ ለማክበር እና የነገውን አረንጓዴ አውሮፕላን ማረፊያ ዛሬ ለመገንባት ያስችላል።

እነዚህ ሳይንሳዊ አካሄዶች የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ከማሳካት ባሻገር የዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ተቋማትን ጥብቅ የአካባቢ ጥበቃ መስፈርቶች ያሟላሉ።

በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች፣ በላቀ የአፈጻጸም ብቃት እና በዓለም አቀፍ ደረጃዎች እየተመራ የሚገኘው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ የምታበረክተው የዘላቂ ልማት እና የአፍሪካ ብልጽግና ሕያው ማሳያ ሆኖ በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነባ ይገኛል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: