የከርሰ ምድር ሀብትን አውጥቶ በቴክኖሎጂ በማበልጸግ ረገድ ኢትዮጵያ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የሺህ ዓመታት የዳበረ ሥልጣኔ ባለቤት ናት።
በአክሱም ሥርወ መንግሥት ዘመን ሀገራችን የራሷን የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሳንቲሞች አትማ ለዓለም አቀፍ ንግድ ታቀርብ ነበር። በጥንቱ ዓለም ከነበሩ እንደ ሮም፣ ፋርስ እና ቻይና ካሉ ታላላቅ ኃያላን መንግሥታት ጋር እኩል የንግድና የኢኮኖሚ የበላይነትም ነበራት።
የጥንቱ የማዕድን አጠቃቀምና የብረታ ብረት ማቅለጥ ጥበብ ለዘመናት በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ ቆይቷል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ በመደመር መንግሥት አዲስ የኢኮኖሚ ሪፎርም አማካኝነት ያንን ታላቅ የሥልጣኔ ታሪክ በዘመናዊ አሠራር የማደስ ጉዞ ተጀምሯል።
የማዕድን ዘርፉን የኢኮኖሚው ዋነኛ ምሰሶ በማድረግና ዘርፉን ከነበረበት ኋላቀር አሠራር በማውጣት ዘመናዊ ፖሊሲዎችና የሕግ ማዕቀፎች ተግባራዊ ተደርገዋል።
በተለይም የማዕድን ሀብት ክምችትን በሳተላይትና በዘመናዊ ጂኦሎጂካል ጥናቶች በመለየት፣ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ ሰፊ የኢንቨስትመንት በር ተከፍቷል።
የአክሱም ሥልጣኔ ወርቅና ብርን በጥሬው ከመሸጥ ይልቅ ወደ ሳንቲምነት ቀይሮ ለንግድ እንዳቀረበው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅትም ማዕድናትን በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምራ ለማቅረብ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች።
በሕገ ወጥ የወርቅ ንግድ ላይ በተወሰደው ጠንካራ እርምጃ እንዲሁም ለባህላዊ እና ዘመናዊ አምራቾች በተደረገው የገበያ ማበረታቻ፣ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በታሪክ ከፍተኛውን መጠን በመያዝ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ለዚህ በዘመናዊ መንገድ ወርቅ የማምረት ሽግግር ተጨባጭ ማሳያ የሚሆነው ግዙፉ የኩርሙክ ጎልድ ማይን የወርቅ ምርቱን በይፋ ለማምረት የመጨረሻ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መገኘቱ ነው።
በአክሱም ዘመን የነበረው የማዕድን ሀብት አጠቃቀም ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ገናና እንዳደረጋት ሁሉ፣ ዛሬ በመደመር መንግሥት የተጀመረው ዘመናዊ የማዕድን ልማትም ኢትዮጵያን ከተረጂነት አላቅቆ ወደ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት የሚያሸጋግር ድልድይ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ከሺህ ዓመታት በፊት በወርቅ ሳንቲሞቿ የዓለምን ገበያ የመራችበትን የቀደመ ታሪክ ዛሬ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በግዙፍ የማዕድን ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እና በተቀናጀ የልማት አመራር በማደስ የታሪኳን ቀጣይነት በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: