Search

የCOP32 ሚስጥር፡ ከፓቪሊዮን ተከራይነት ወደ ዓለም ቤትነት

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 83

ኢትዮጵያ ለዓመታት ወደ ዓለም አቀፍ የኮፕ (COP) ጉባኤዎች ስትጓዝ አንድ ጠባብ ድንኳን ተከራይታ፣ ድምጿን ለማሰማት ወረፋ ትጠብቅ ነበር።

ዛሬ ግን ያ የዳር ተመልካችነት ዘመን አብቅቶ ታሪክ ተቀይሯል። ከዱባይ እስከ ባኩ እና ቤሌም በተካሄዱት መድረኮች ኢትዮጵያ አንድ ወሳኝ እውነታ ተገንዝባለች፤ የዓለም የአየር ንብረት ፖለቲካ የሚወሰነው በስብሰባ አዳራሾች ንግግር ብቻ ሳይሆን አስተናጋጇ መንግሥት በመሬት ላይ በምታሳየው ተግባራዊ ሞዴል ነው።

የመደመር መንግሥት ይህንን እውነታ በጥልቀት በመረዳት፣ ሀገራዊ አቅሞችን አስተባብሮ ኢትዮጵያን ከተሳታፊነት ወደ ዓለም አቀፍ የመፍትሔ ማዕከልነት እና ባለቤትነት አሸጋግሯታል።

ቀደም ሲል በርካታ መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤን ያዘጋጁት በነዳጅ ሀብታቸው ላይ ተቀምጠው ስለ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየሰበኩ ነበር። ኢትዮጵያ ግን ይህንን ታሪካዊ ተቃርኖ በተግባር ሰብራዋለች።

በነዳጅ የሚሰሩ የቤት ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማገድ ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ለ32ኛው ጉባኤ እንግዶቿ የምታቀርበው በወረቀት ላይ የሰፈረ ፖሊሲ ሳይሆን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የሚሽከረከር የሚታይ ማስረጃ ነው።

በኮሪደር ልማት የተዋቡት ሰፋፊ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች፣ ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና ዘመናዊ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ጋር ተዳምረው መዲናችንን የዘመናዊ አረንጓዴ ከተሜነት ተምሳሌት አድርገዋታል።

ሌላው ትልቁ እመርታ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ለውጥ ነው። ኢትዮጵያ ከእርዳታ ጠያቂነት ተላቅቃ በመደመር እሳቤ በተመራው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 56 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ ተራሮቿን እና መልክዓ ምድሮቿን መልሳ አልብሳለች።

ይህ አስደናቂ ስኬት በዓለም መድረክ የካርቦን ገበያ ተዋናይ እና የመፍትሔ አጋር ሆና በልበ ሙሉነት እንድትደራደር አስችሏታል።

ከዚህም ባሻገር በበጋ መስኖ ስንዴ እና በሌማት ትሩፋት የተመዘገቡት የምግብ ሉዓላዊነት ድሎች፣ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅሟ በተግባር የተፈተነ እና ለአፍሪካም አርአያ የሚሆን መሆኑን በጉልህ ያረጋግጣሉ።

በኮፕ ጉባኤዎች የሚፈስሰውን የቢሊዮን ዶላሮች የኮንፈረንስ ኢኮኖሚ እና የቱሪዝም ገቢ በሀገር ውስጥ እንዴት ማስቀረት እንደሚቻልም ከቀደሙት አስተናጋጆች ልምድ በመውሰድ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል።

በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የተገነቡት የወዳጅነት፣ የእንጦጦና የአንድነት ፓርኮች እንዲሁም ግዙፉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አዲስ አበባን ተመራጭ የዲፕሎማሲና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል አድርገዋታል።

ከወንዝ ዳርቻ ልማቶች ጋር የተሳሰሩት እነዚህ መሠረተ ልማቶች፣ እንግዶች ተፈጥሮ እና ዘመናዊነት የተዋሃዱባትን ውብ እና አዲሲቷን ኢትዮጵያ በዓይናቸው እንዲያዩ ልዩ ዕድል ይፈጥራሉ።

በኮፕ 32 ዓለም ወደ አዲስ አበባ ሲተም፣ ስብሰባ የሚቀመጠው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና በሌሎችም ግዙፍ ፕሮጀክቶች አማካኝነት 100 በመቶ በታዳሽ ኃይል በምትደምቅ ከተማ ውስጥ ነው።

ይህ የዓመታት የኮፕ ተሳትፎ ልምድና የመደመር መንግሥት ቁርጠኛ አመራር የወለደው አዲስ ታሪክ ነው።

ኢትዮጵያ የዓለምን የአየር ንብረት ጉባኤ የምታስተናግደው በባዶ ቃላት ሳይሆን ራሷን የነገዋ አረንጓዴ ዓለም ማሳያ አድርጋ በማቅረብ ነው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: