Search

ኢትዮጵያ ገና አልተነካችም፤ የጀመርናቸው ሥራዎች መልካም ጅማሮዎች ቢሆኑም ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 14

በአዲስ አበባ የተጀመሩት የኮሪደር ልማት ሥራዎች በርካታ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ የንግድ እንቅስቃሴን በማነቃቃት እና የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለነዋሪዎች አዳዲስ ዕድሎችን ይዘው መምጣታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በከተማዋ የታየው የሕንፃዎች እና የሰፈሮች መሻሻል ለተመልካች ደስታን እና ጤናን የሚሰጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያፋጥን መልካም ጅማሮ መሆኑን አንስተዋል።

የተገኙት ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም፣ ሀገራችን ያላት እምቅ አቅም ገና ያልተነካ በመሆኑ የእርካታ ስሜት ሊሰማን እንደማይገባ አሳስበዋል።

ሀገርን መገንባት የሚቻልበት ትክክለኛ አቅጣጫ በግልጽ መታየቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በመዲናዋም ሆነ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች አሁንም የመኖሪያ ቤት፣ የመንገድ፣ የፓርኪንግ እና የንግድ ሥርዓት ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ሆኖ ዜጎች ያለምንም እጅ መንሻ የሚስተናገዱበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ገና ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የተሠሩ መልካም ሥራዎች ቀሪ የቤት ሥራዎቻችንን እንዳይሸፍኑብን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በዚሁ አግባብ ተግተን ከሠራን በመጪዎቹ አሥር ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ ዘመናዊ ከተሞች እንደሚፈጠሩ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከአዲስ አበባ ውጭ በሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ጅማ፣ ሐረር፣ ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ነቀምት ከተሞች እየመጣ ያለው የልማት ለውጥ ቀላል አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ከተሞች ለሥራ፣ ለመዝናኛ እና ለተለያዩ ሁነቶች ምቹ እየሆኑ መምጣታቸውን በመግለጽ፣ አርባ ምንጭ ከተማን ለዚህ እንደ አብነት አንስተዋል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: