በአዲስ አበባ ከተማ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ተነስቶ በምስራቅ አጠቃላይ፣ በሃያ ሁለት እና በጎላጉል አልፎ እስከ ቦሌ መድኃኔዓለም የሚዘልቀው የኮሪደር ልማት ስራ ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃው ወቅት እንደገለጹት ይህ ፕሮጀክት ለመዲናችን ተጨማሪ ውበትና ጌጥ የሆነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ሥራ ነው።
በኮሪደሩ ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች፣ ሰፋፊ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጂንግ ጣቢያዎች መገንባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በተጨማሪም የአካባቢው ነዋሪዎች እና ጎረቤቶች ወጥተው የሚንቀሳቀሱበት፣ የሚዝናኑበት፣ ልጆች የሚጫወቱበት እንዲሁም ስፖርታዊ ውድድሮችን የሚመለከቱበት ምቹ ስፍራ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በውጭ ሀገራት ብቻ ታይተው የሚቀናባቸውን የከተማ ልማት ደረጃዎች በኢትዮጵያ እውን ማድረግ መቻሉንም አስምረውበታል።
ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታም በድጋሚ መጀመሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ስታዲየሙ ከስድስት እስከ ሰባት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም የተጨናነቁ እና ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ የነበሩት የአደይ አበባ እና የቺቺንያ አካባቢዎች ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ ገጽታቸው ተቀይሮ ለነዋሪዎች ምቹና ክፍት የመዝናኛና የስፖርት ማዕከል መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: