Search

ኢትዮጵያ ለCOP32 ዝግጅት ከተመድ የአካባቢ ፕሮግራም ጋር ያላትን ትብብር እያጠናከረች ነው

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 95

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የCOP32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ በቱርክ አንታልያ እየተካሄደ ካለው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) ጎን ለጎን ከተመድ የአካባቢ ፕሮግራም (UNEP) ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታስተናግደው 32ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) እየተደረጉ ባሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ዙሪያ በስፋት መክረዋል።

በተለይም የተቋሙ የበካይ ጋዝ ልቀት ክፍተት (Emissions Gap) እና ለአየር ንብረት ለውጥ የመጣጣም ክፍተት (Adaptation Gap) ሪፖርቶች የCOP32 ዝግጅቶችን በሳይንሳዊ መረጃ እንዴት ሊደግፉ እንደሚችሉ እንዲሁም የመጣጣም ክፍተቱን ለመሙላት የሚያስፈልጉ የፋይናንስ እና ሌሎች ሀብቶችን ማሰባሰብ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።

ሁለቱ አመራሮች በአፍሪካ ታዳሽ ኃይልን በስፋት ማልማት እና ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ተወያይተዋል።

ከዚህ ባለፈም እንደ ከፍተኛ ሙቀት ያሉ ከባድ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የከተሞችን ተቋቋሚነት ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የUNEP ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን በበኩላቸው፣ የCOP32 ፕሬዚዳንትነት ለአዲስ አበባ ጉባኤ የሚያስቀምጣቸውን ቅድሚያ የሚሰጣቸው አጀንዳዎች በሚቀርጽበት ሂደት ተቋማቸው አስፈላጊውን ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማበርከት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: