Search

ኢትዮጵያ የወረርሽኝ ዝግጁነትና የምላሽ አሰጣጥ አቅሟን አሳድጋለች - ጤና ሚኒስቴር

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 65

ኢትዮጵያ የወረርሽኝ ዝግጁነትን ከዕቅድ ወደ ተግባር በመቀየር፤ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪዎችን በማደራጀትና የጤና ሥርዓቷን በማጠናከር ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗን የወረርሽኝ መከላከል ዝግጁነትና ምላሽ (EPPR) ፕሮጀክት የአስተዳደር ቦርድ አስታወቀ።

የጤና ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የመንግሥት ተቋማት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፕሮጀክቱ የአስተዳደር ቦርድና የፈንድ አስተዳደር ስብሰባ መካሄድ ጀምሯል።

የወረርሽኝ በሽታዎችን በቅድሚያ ለመከላከል ለሚያጋጥሙ የጤና ስጋቶች ዝግጁ ለመሆንና ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት ያለመው ይህ ስብሰባ በዋናነት በአንድ ጤና (One Health) አካሄድ ላይ ትኩረት በማድረግ በፕሮጀክቱ አፈጻጸም የተገኙ ተሞክሮዎችን ውጤቶችንና ስኬቶችን ለመገምገም ያለመ ነው።

ኢትዮጵያ የወረርሽኝ ዝግጁነትን በማጠናከር ረገድ ጠንካራ አመራርና ቁርጠኝነት ማሳየቷ በመድረኩ ላይ የተገለጸ ሲሆን በተለይም እንደ ማርቨርግ ኢቮላ እና መሰል ወረርሽኞችን ለመከላከል ያደረገችው ቅድመ ዝግጅትና ጥረት አርአያነት ያለው መሆኑ ተመላክቷል።

ከዚሁ ባለፈ ኢትዮጵያ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በአንድ ጤና (One Health) ማዕቀፍ የበሽታ ክትትልን የላቦራቶሪ አቅምን የሰው ኃይል ብቃትንና የአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥን ለማጠናከር ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ተጠቅሷል።

የቦርዱ አመራሮችም ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ቀድሞ ለመከላከል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ያለውን ሥራ አድንቀዋል።

በመርሐ ግብሩ ጎን ለጎን የቦርዱ አመራሮች በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ጤና ደኅንነትን ለማረጋገጥ እየገነባ ያለው ተቋማዊ አቅምና በፕሮጀክቱ የተመዘገቡ ውጤቶች እጅግ የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የፓንደሚክ ፈንድ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመሀሪ አለሙ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: