Search

የከተማ ልማት ጥራት የአንድ ሀገር ምርታማነት መገለጫ እየሆነ መጥቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 48

የከተማ ልማት ጥራት የአንድን ሀገር ምርታማነት፣ የሰው ልጅ ክብር፣ ማኅበራዊ ሥርዓት እና የአካባቢን ችግር የመቋቋም ዐቅም መገለጫ እየሆነ መጥቷል።

በመሆኑም የመደመር መንግሥት የከተሜነት ዕሳቤ፣ ከተሞችን የሥራ ፈጠራ፣ የንግድ፣ የዕውቀት፣ የባህል፣ የተቋማት እና የሥራ ዕድል ምርታማነት ማዕከላት እንዲሆኑ ያደርጋል።

ይህም ለወደፊት የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ክስተቶች፣ ለመሠረተ ልማት ፍላጎቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ በዕቅድ የተዘጋጀ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ይፋ በተደረጉት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ በመመሥረት የተከናወነ ተጨማሪ 57 ሄክታር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ዛሬ በይፋ መርቀው ከፍተዋል።

ይህም ከቦሌ መድኃኔዓለም በጎላጉል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ፣ ከቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ሞኤንኮ፣ ከቦሌ ትምህርት ቤት እስከ አደይ አበባ ሞዴል መንደር፣ ከኢምፔሪያል ሆቴል እስከ ሻላ ፓርክ፣ ከቺቺኒያ እስከ ቦሌ ሩዋንዳ፣ ከአደይ አበባ ስታዲየም እስከ ቦሌ መንገድ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ያካትታል።

ለአረንጓዴ እና ዘመናዊ የከተማ ልማት አዲስ መሥፈርት የሚያስቀምጠው ይህ ፕሮጀክት፣ ዘመናዊ መንገዶችን፣ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶችን፣ የብስክሌት መሥመሮችን፣ የመሬት ውስጥ መሠረተ ልማቶችን፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን እና ከ5,000 በላይ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችሉ የመኪና ማቆሚያዎችን ያካትታል።

በተጨማሪም የታደሱ ትምህርት ቤቶችን፣ ቤተ መጻሕፍትን፣ የመጨዋቻ ሥፍራዎችን፣ የስፖርት ሜዳዎችን፣ ካፌዎችን፣ ሬስቶራንቶችን እና ፕላዛዎችን የያዘ ሲሆን፣ ሰዎችን፣ ሰብአዊ ክብርን እና የኑሮ ጥራትን የከተማ ልማት ዋነኛ ማዕከል አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው እንዳሉት፣ ይህ ከመሠረተ ልማት ግንባታ በላይ ነው፤ ለአዲስ አበባ እና ለኢትዮጵያ ከተሞች መጻኢ ዕድል የተነደፈ ሰፊ ራዕይ አካል ነው፤ ይኸውም ምርታማትን፣ አካታችነት፣ አረንጓዴነትንና የማይበገር ልማትን  ያካተተ ነው። ክንውኑም በሕዝቦቻችን ፍላጎት እና በመጪው ትውልድ መሻት ዙሪያ የተቃኘ ነው።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: